ቀጥታ፡

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ተሻግረው በአፍሪካ ገበያ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን አበርክቶ ይበልጥ በማጠናከር  ከኢትዮጵያ ተሻግረው በአፍሪካ ገበያ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ‎መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

በ2014 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ 41 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ አንድ በመሰብሰብ የኢትዮጵያን ሃብት የማወቅ፣ ተበታትኖ የቆየውን ሃብት በተደራጀ መንገድ የማስተዳደር ስራ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።

ተቋሙ ከመመስረቱ አስቀድሞ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ፣ የኦዲት፣ የካፒታል፣ የብድር ጫና እና የኮርፖሬት አስተዳደር ችግር ውስጥ የነበሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ኢንቨትመንት ሆልዲንግስ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች ዘመናዊ የባለቤትነት፣ የአስተዳደር ስርዓት እና ዓለም አቀፍ የኮርፖሬት አስተዳደር ስርዓት ተዘርግቶላቸዋል ብለዋል። በተጨማሪም ዘመናዊ የኦዲት ስርዓት እንዲከተሉ መደረጉንም አስታውቀዋል።

‎‎ይህም ተቋማቱ ከኪሳራ ወጥተው ወደ ትርፋማነት እንዲሸጋገሩ አስችሏል ነው ያሉት። ባለፉት አራት ዓመታትም የተቋማቱ አጠቃላይ ገቢ ቀድሞ ከነበረበት ከ704 ቢሊየን ብር ወደ 6.1 ትሪሊየን ብር ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ዛሬ ላይ በ36 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በእነዚህ ተቋማት ስር ያለው የሃብት መጠንም 8.2 ትሪሊየን ብር መድረሱን አስታውቀዋል።

በዚህም የመንግስት የልማት ድርጅቶች በኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን አበርክቶ ይበልጥ በማጠናከር ከኢትዮጵያ ተሻግረው በአፍሪካ ገበያ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ነው ማለታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም