ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018 (ኢዜአ)፡- ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ የ14 ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል።
የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንት ታዬ ያቀረቡት፤ የደቡብ ሱዳን፣ ጣልያን፣ ሞሪሺየስ፣ ዛምቢያ፣ ጀርመን፣ ጆርዳን፣ ኒውዝላንድ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሞዛምቢክ፣ ኬንያ፣ ቤላሩስ፣ ፊሊፒንስ፣ ኪርጊስታን እና የላቲቪያ አምባሳደሮች ናቸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት ማብራሪያም፤ የሹመት ደብዳቤያቸውን ካቀረቡ ሀገራት መካከል 11ዱ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበበት ባለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም ሀገሮቻቸው በንግድ እና ኢንቨስትመንት በሚሰማሩባቸው መስኮች ላይ አምባሳደሮቹ ከፕሬዚዳንት ታዬ ጋር መወያየታቸውንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች በሚያስከብሩ ሥራዎች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በውይይቱ አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ ማድነቃቸውንም አንስተዋል።
በኢትዮጵያና በሀገራቱ መካከል የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል ነው ያሉት።