ዘርፉ ኢኖቬሽን እና ስራ ፈጠራን በመደገፍ ለሃገራዊ እድገቱ የበኩሉን እንዲወጣ ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ዘርፉ ኢኖቬሽን እና ስራ ፈጠራን በመደገፍ ለሃገራዊ እድገቱ የበኩሉን እንዲወጣ ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ ዘርፉ ኢኖቬሽን እና ስራ ፈጠራን በመደገፍ ለሃገራዊ እድገቱ የበኩሉን እንዲወጣ ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኹልቁ ገለጹ፡፡
ሃገራዊ ለውጡ ለኢኮኖሚው ስርዓት ካስተዋወቃቸው ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን አንዱ ነው።
ይህ ባለስልጣን የካፒታል ገበያ ስርዓትን ፈጠራን በማበረታታት በካፒታል ፈላጊዎች እና ካፒታል አቅራቢዎች መካከል ድልድይ የሚሆን ስርዓት እየገነባ መሆኑ ተመላክቷል።
በኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም በሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው የካፒታል ገበያ ስርዓት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ ሶስት ቁልፍ ተቋማትን መፍጠር መቻሉን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኹልቁ ተናግረዋል።
እነዚህም የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ እና የማዕከላዊ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ግምጃ ቤት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እነዚህ ተቋማት ከማቋቋም ባለፈ የካፒታል ገበያ አገልግሎት የሚሰጡ 15 ተቋማት ፈቃድ አግኝተው ወደ ስራ መግባታቸውንም አስታውቀዋል።
ተቋማቱም የተከፈለ ካፒታላቸው 1.5 ቢሊየን ብር መድረሱን እና በተጨማሪም 10 ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋይ ገበያ ላይ ለመመዝገብ ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በባንኮች መካከል በገበያ ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ልውውጥ እያደገ መጥቷልም ብለዋል። በቀጣይ ዘርፉ ኢኖቬሽን እና ስራ ፈጠራን በመደገፍ ለሃገራዊ እድገቱ የበኩሉን እንዲወጣ ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።