ቀጥታ፡

የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስታት የቅርስ ዕድሳትና የልማት ሥራዎች አስደናቂ ናቸው 

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስታት የቅርስ ዕድሳትና የልማት ሥራዎች አስደናቂ መሆናቸውን የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክና የሀገር ሽማግሌዎች በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች እና በቅርሶች ጥበቃ መደመማቸውንም ገልጸዋል።

የፌዴራልና የክልል መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታትን ጎብኝተዋል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን የመጡት የሀገር ሽማግሌ እያሱ ገጀቦ፤ በጎንደር ከተማ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላችው ገልፀው፤ በከተማዋ የተመለከቱት ልማት እና የቅርስ ጥበቃ ስራ አስደናቂ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጋራ ታሪክ የሆነውን የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስታት እንዲታደስ ለወሰዱት ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የመጡት ሀደ ሲንቄ ሸምስያ ጉተማ በበኩላቸው፥ የጎንደር ጉብኝታቸው ሕብረ ብሔራዊ የጋራ ታሪካችንን፣ ሃብትና የጠበቀ ትስስራችንን እንድንገነዘብ አድርጎናል ብለዋል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚከናወኑ የኪነ-ጥበብ ስራዎችም ሕብረ-ብሔራዊና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን የመጡት የሀገር ሽማግሌ ዳሞ በለጠ እንዳሉት፥ በጎንደር ከተማ የተከናወነው አስደማሚ ሥራ መንግስት የሀገር ሀብት እና ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችም አምሮና ተውቦ የታደሰውን አብያተ መንግስታት እንዲጎበኙ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከአፋር ክልል የመጡት የሀገር ሽማግሌ አቢቶ ዑሙካ በሰጡት አስተያየት፤ በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችና የፋሲል አብያተ መንግሥታት ቅርስ ጥበቃ ሥራ አስደማሚ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል።

በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልም መደሰታቸውን ነው የተናገሩት።

በቆይታቸውም የተመለከቱትን የጋራ የታሪክ እሴትና የቅርስ ጥበቃ ተሞክሮ ለአፋር ሕዝብ እንደሚያካፍሉ ገልጸዋል።


 

የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክ አባል አርቲስት አደም ሙሀመድ፥ በጎንደር ከተማ በመጀመሪያ ጉብኝቱ ወቅት የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስታት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት መመልከቱን አስታውሶ፤ በአሁኑ ወቅት ታድሶ በማየቱ መደሰቱን ተናግሯል።

የቅድመ አያቶች የጋራ የታሪክ አሻራ ያረፈበትን የጎንደር አብያተ መንግስታትም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች ምቹ ሆኖ መታደሱን ገልጿል።

ሌላኛዋ የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክ አባል አርቲስት ርብቃ ጉዴ፤ ከዚህ ቀደም በታሪክ የምታውቀውን የጎንደር ታሪካዊ ቦታ መጎብኘቷ ልዩ ስሜት አለው፥ ሌሎችም ሊጎበኙት ይገባል ብላለች።

የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክ የባህል ቡድን አሠልጣኝ አርቲስት ወንድዬ ኮንታ፤ ጎንደር የኢትዮጵያዊያን ሥልጣኔ መሠረት መሆኗን የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስታት መገለጫ ናቸው ብሏል።

የኪነ-ጥበብ ሥራ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር መሠረት በመሆኑ በቀጣይነት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጿል።

በቀጣይም ሰላምን ማጽናት የሚያስችል የምክክር ዕድል በማመቻቸትና ወንድማማችነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።

የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ አመሻሽ ላይ በጎንደር ከተማ መስቀል አደባባይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር የባህልና የኪነ-ጥበብ ስራ ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም