በሱማሌ ክልል የእናቶችን ጤና ለማሻሻል የግንዛቤ ማሳደግ ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በሱማሌ ክልል የእናቶችን ጤና ለማሻሻል የግንዛቤ ማሳደግ ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል
ጅግጅጋ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦በሱማሌ ክልል የእናቶችን ጤና ለማሻሻል የግንዛቤ ማሳደግ ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ ገለጹ።
ጥር የጤናማ እናትነት ወር “ፈጠራ እና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት!” በሚል መሪ ሐሳብ በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተከበረ።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤የጤናማ እናትነት ወርን ስናከብር የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ የሚያግዙ የግንዛቤና ሌሎች ተግባራትን በትኩረት በመከወን መሆን አለበት።
ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የካራማራ አጠቃላይ ሆስፒታል የእናቶችና የህጻናት ማዕከል የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እናቶች በጤና ተቋሟት በመውለድ የራሳቸውን ጤና ከመጠበቅ ባለፈ ጤናማ ትውልድን ለማስቀጠል ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ የእናቶችን ጤና የመጠበቅ ሥራ የአንድ ወቅት ሥራ አለመሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማሻሻልና በየጊዜው አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር የእናቶችን ጤና ማሻሻል እንደተቻለም ገልጸዋል።
መንግስት በጤና ተቋማት ማስፋፊያና ግንባታ፤ በሠዉ ሃይልና ግብዓትን በማሟላት ረገድ ሰፋፊ ስራዎች እያከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፤ የእናቶች ሞትን ለመቀነስ በተደረገው ጥረት እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ የተቋማቱን ተደራሽነት ማስፋት ላይ የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም የእናቶች ሞትን በከፍተኛ ደረጃ የመቀነሱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የጤና ተቋማትን ጥራት ለማረጋገጥና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በመድረኩ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።