ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የኪነጥበብ ሥራዎች ወሳኝ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የኪነጥበብ ሥራዎች ወሳኝ ሚና አላቸው
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያውያንን የባህል ትስስር በማጉላት ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የኪነጥበብ ሥራዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
የፌደራልና የክልል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች በጎንደር የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፥ በዜጎች መካከል ሕብረ-ብሔራዊ የባህልና ዕሴት ትስስርን ለማጠናከር የኪነጥበብን ሚና በመጠቀም ረገድ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የወከሉ ከያኒያንን ያካተተው የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በሚያጠናክር መልኩ የኢትዮጵያን ባሕልና ዕሴት በቻይና፣ ሩሲያና ጃፓን በማቅረብ ለዓለም ህዝብ ማስተዋወቁን አንስተዋል።
የባህል ልዑኩም የኢትዮጵያን ቱባ ባህልና ዕሴቶች ለዓለም በማሳየት እና የመስህብ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ የሀገር የገጽታ ግንባታ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል።
የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች የአፄ ፋሲለደስ አብያተመንግስትና የጎንደር የልማት ሥራዎችን እንደጎበኙ አንስተዋል።
የመጀመሪያው የሀገር ውስጥ የኪን-ኢትዮጵያ ጉዞ በጎንደር የባህልና የኪነ-ጥበብ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማብሰሪያ መድረክ እንደሚካሄድም ገልጸዋል።
በቀጣይም የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክ በኢትዮጵያ ከተሞችና በጎረቤት ሀገራት የኪነ-ጥበብ ሥራን በማቅረብ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚሰራ አብራርተዋል።