በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ ምርትና ምርታማነትን አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ ምርትና ምርታማነትን አሳድጓል
ሮቤ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦በባሌ ዞን ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የዞኑ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በዞኑ የ2018 የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በጎሮ ወረዳ ወልተኢ ጨፋ ቀበሌ ደራርቱ ተፋሰስ ላይ ዛሬ ተጀምሯል።
ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል አህመድ መሐመድ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተራቆቱ መሬቶች መልማታቸው የንብ ማነብ ሥራን ለማከናወንና ምርታማነትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።
በዘንድሮ የበጋ ወቅትም ከአምናው የተሻለ የልማት ሥራ ለማከናወን ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን አመልክተዋል።
በተፋሰስ ልማት ስራ የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል ባለፈ ደርቀው የነበሩ ምንጮች መልሰው መመንጨት ጀምረዋል ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ሀሰን አብዶ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በለሙ ተፋሰሶች ውስጥ የተተከሉ እጽዋቶች በመጽደቃቸውና እርጥበታማ አየር እንዲኖር በማስቻሉ የግብርና ስራን በተሻለ መልኩ በማከናወን ድርቅን ለመቋቋም እያገዛቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።
አርሶ አደር ሐምዛ ቃዲ በበኩላቸው እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በተፋሰስ ልማት ሥራ በተሰሩ ሥራዎች ከምርት ውጭ ሆኖ የነበረ የእርሻ መሬታቸው በማገገሙ እስከ 40 ኩንታል የስንዴ ምርት ማግኘት ችለዋል።
አርሶ አደሮቹ እንዳሉት የተፋጥሮ ኃብት ጥበቃና የእንክብካቤ ሥራን በማጠናከር ምርታማነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው ይቀጥላሉ።
የጎሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ እሸቱ ተክሌ በበኩላቸው፣ በወረዳው ባለፉት ዓመታት በቅንጅት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የአካባቢውን አየር ንብረት ከማስተካከል ባሻገር ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የተፋሰስ ልማት ሥራ የአፈር ለምነት በመጨመሩ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን የገለጹት ደግሞ የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉአድ ናቸው፡፡
በዘንድሮው የበጋ ወራትም ሥራውን በተቀናጀ መንገድ አጠናክሮ በማስቀጠል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ከ549 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ በሚካሄደው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትም በ166 ተፋሰሶች ላይ ከ84 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ስነ አካላዊ ስራዎች ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ሴይፋዲን ሀሰን፤ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያበረክተው ጠቀሜታ በተጨማሪ ለቀጣዩ ትውልድ የለማና አረንጓዴ ሀገርን የማስረከብ ዓላማ ያለው በመሆኑ ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።