የክልሉን የልማት አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ሰላምን ማጽናት ቀዳሚ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን የልማት አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ሰላምን ማጽናት ቀዳሚ ተግባር ነው
አዲስ አበባ፤ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ያለውን ሰፊ የልማት አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር በሁሉም አካባቢዎች ሰላምን ማጽናት ቀዳሚ ተግባር በማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) ገለፁ።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ትብብር የተዘጋጀው የፓናል ውይይት "ሰላምን ማጽናት፤ፀጋን ለማልማት"በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) በክልሉ የተከናወኑ "የሰላምና ፀጥታ ስራዎችና እምርታዎች" በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በጽሁፋቸው በክልሉ ሰላምን ለማጽናት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተገኙ የሰላም እመርታዎችን ጠብቆ ማስቀጠል ለልማት ስራዎች መሳካት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
የህዝቡን ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች በክልሉ ልማትን ለማፋጠን ወሳኝ በመሆናቸው ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ክልሉ ያለውን ሰፊ የልማት አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር በሁሉም አካባቢዎች ሰላምን ማጽናት ቀዳሚ ተግባር በማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፤ "የክልሉ ፀጋዎችና የኢንቨስትመንት አማራጮች” በሚል ርዕስ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በጽሁፋቸውም ክልሉ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑና ያልተነኩ በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ለማዕድን፣ ለቱሪዝም፣ ለእንስሳት ሀብት ልማት፣ ለውሃ እና ለመሬት ልማት ምቹ የሆኑ በርካታ ዕድሎች መኖራቸውን አብራርተዋል።
የክልሉ የሥነ-ምህዳር አወቃቀርና ምቹ የአየር ንብረት ለግብርና ዘርፍ ዕድገት እምቅ አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት የተመዘገቡ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ተፈጥሯዊ መስህቦች እና የማይዳሰሱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች የክልሉ የቱሪዝም ሀብት መገለጫ ናቸው ብለዋል።
እነዚህን ሀብቶች በተገቢው መንገድ በማልማት የቱሪዝም ዘርፉን የኢኮኖሚ ምሰሶ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በክልሉ የሚገኙ የከበሩ ማዕድናት፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች እና ለኢንዱስትሪ ልማት አመቺ ሁኔታዎች ለኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህን የተፈጥሮ ፀጋዎችና የኢንቨስትመንት አማራጮች በአግባቡ በመጠቀም የክልሉን አልፎም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ ይቻላል ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ የግል ባለሀብቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት የክልሉ መንግስት ለባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው "የአማራ ክልል የልማት ተስፋዎችና የህዝብ ተጠቃሚነት" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ ክልሉ የረጅም፣ የመካከለኛ እና የአጭር ዘመን እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።
በዚህም በ2027 የአማራ ክልል በመሠረታዊ ኢንዱስትሪ ምርቶች የራሱን ፍላጎት የሸፈነ እና የተሳካ የመዋቅራዊ ሽግግር በማድረግ የክልሉን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ በማቀድ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በ2042 ክልሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ የሆነ የዘመናዊ ኢኮኖሚ ባለቤት እና የበለጸገ ማሕበረሰብ ሆኖ ማየት የዕቅዱ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የክልሉን ሠላምና ደህንነት እንዲሁም የህግ የበላይነት ማረጋገጥ፤ የተቋማትን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም መገንባት ስትራቴጂክ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ክልላዊ ወጎችን፣ ዕሴቶችን እና ባህሎችን በማዳበር በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራትንም እንዲሁ።
በተጨማሪ ሣይንሳዊ ዕውቀትን የማሕበረሰብ እሴት እና የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ማድረግ፤ ምርታማነትንና ቅልጥፍናን በማሳደግ ጥራት ያለው ኢኮኖሚ መገንባት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡