በመዲናዋ የተገነቡ የልማት ስራዎችን የመጠበቅና የመንከባከብ ሃላፊነት የሁላችንም ነው-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የተገነቡ የልማት ስራዎችን የመጠበቅና የመንከባከብ ሃላፊነት የሁላችንም ነው-ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የተገነቡ የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማቶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ሃላፊነት የሁላችንም ነው ሲሉ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
አዲስ አበባን ዘመናዊ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተከናወኑ ከሚገኙ ስራዎች መካከል የወንዝ ዳርቻ ልማት አንዱ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቅርቡ የቀበናና ግንፍሌ ወንዝ ዳርቻ ልማት ሂደትን በተመለከቱበት ወቅት እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቶቹ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸውን ከስጋትና ከብክለት ነጻ በማድረግ ስነ-ምህዳሯን የጠበቀች፤ ውብና ፅዱ ከተማ ለመፍጠር እያስቻሉ ነው፡፡
በከተማዋ ተረስተው የነበሩና ከልማት ተገልለው የቆዩ የወንዝ ዳርቻዎች ዛሬ ላይ የብዙዎች አይን ማረፊያና ምቹ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ሆነው መልማታቸውን ገልጸዋል፡፡
የልማት ስራዎቹ እንደ ከተማም ሆነ እንደ ሀገር አዲስ እሳቤና ምሳሌ መሆናቸውን አንስተው፤ ፕሮጀክቶቹ ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ውጤት ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
ይህንኑ አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችና የኮሪደር ልማቶች የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ ከመቀየራቸው በላይ ለነዋሪዎች የመዝናኛ አማራጭ ሆነዋል፡፡
በከተማዋ በቀጨኔ ወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት ሲዝናኑ ያገኘናቸው አቶ መሀመድ ተመስገን፤ አካባቢው ከዚህ ቀደም ለወንጀል ምቹ የሆነ፣ ለጎርፍ የተጋለጠና ለማየት የማይመች እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በአካባቢው ለረጅም ጊዜ ከመኖራቸው አንጻር የወንዙ ዳርቻ በዚህ ደረጃ ተለውጦ መመልከታቸው እንዳስገረማቸው ተናግረዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ካሳዬ፤ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት የተበከሉና ቆሻሻ መጣያ የነበሩ ወንዞችን ያከመና ወደ ቀደመ ማንነታቸው የመለስ ነው ብለዋል።
ስፍራዎቹ አሁን ለህጻናት፣ ወጣቶችና አዋቂዎች የመዝናኛ አማራጭ ከመሆን ባለፈ መንፈስን የሚያድሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሂሩት አድነው፤ በወንዝ ዳር የተሰሩ የልማት ስራዎች ወንዞችን ከቆሻሻ መጣያነትና ከመጥፎ ጠረን በማላቀቅ ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፤ በኮሪደር ልማቱ የተገነቡ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ ፓርኮችና የመዝናኛ ስፍራዎች የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ የቀየሩና ለነዋሪዎች የመዝናኛ አማራጭ የፈጠሩ ናቸው፡፡
በመዲናዋ የተገነቡ የልማት ስራዎች የታለመላቸውን አገልግሎት በዘላቂነት እንዲሰጡ የመጠበቅና የመንከባከብ ሃላፊነት ከሁሉም የሚጠበቅ ግዴታ መሆኑን አንስተዋል።