የብልጽግና ፓርቲ እቅድ እና እሳቤዎች ተጨባጭ ውጤት እየተገኘባቸው ነው- አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የብልጽግና ፓርቲ እቅድ እና እሳቤዎች ተጨባጭ ውጤት እየተገኘባቸው ነው- አቶ አደም ፋራህ
ሆሳዕና፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦የብልጽግና ፓርቲ እቅድ እና እሳቤዎች በሁሉም አካባቢዎች እየተተገበሩ ተጨባጭ ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
የፓርቲው የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ሲሆን የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የቀረበው የፓርቲው ሥራ አፈፃፀም የሚያመለክተው የብልጽግና ፓርቲ እቅድ እና እሳቤዎች በሁሉም አካባቢዎች የህዝብ ቅቡልነት በማግኘት እየተተገበሩ ናቸው ብለዋል፡፡
ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ለፓርቲው ስራዎች ውጤታማነት የሚረዳ የተናበበ እቅድ የማዘጋጀት እንዲሁም የፓርቲውን እሳቤ በመረዳት በስነ ምግባር የሚፈፅም ጠንካራ አመራር ለማብቃት በተሰራው ስራ መሻሻሎች መታየታቸውንም ገልጸዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድም ከህዝቡ ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኮሪደር ልማት ስራ እና የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲውን እሳቤዎች በመተግበር ህዝቡ ተባባሪ ሆኖ በመስራቱ ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ልማትን የማፋጠን እና መልካም አስተዳደር የማስፈን ስራዎች አሁንም በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥሉ ገልጸው የህዝቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በፓርቲው የተያዙ ሁሉን አቀፍ የእድገትና ትራንፎርሜሽን አጀንዳዎችን ለማሳካት አመራሩ በትኩረት መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎችና የወጣት ክንፍ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡