ቀጥታ፡

በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ስራ ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል -ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን

አሶሳ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ስራ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

የአሶሳ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው የተሻሻለ የመስኖ አውታር ቴክኖሎጂ ተመርቆ ወደ ስራ ገብቷል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ስራ በማከናወን ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ማፍራት ላይ ማተኮር አለባቸው።

የአሶሳ ግብርና ኮሌጅም በሰለጠኑበት ሙያ ብቁ የሆኑ ሰልጣኞችን ለማፍራት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል። 

ከዚህም በተጨማሪ ኮሌጁ ዘመናዊ የግብርና መካናይዜሽንን በማስፋት አርሶአደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እያከናወናቸው የሚገኙ የምርምር ስራዎች መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።


 

ኮሌጁ የሚያፈልቃቸው አዳዲስ  የግብርና ቴክኖሎጂዎችም የኮሌጁን መማር ማስተማር ስራ ከማገዝ  በተጨማሪ ለአርሶአደሩ ተሞክሮ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

የአሶሳ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ ሙስጠፋ ያሲን በበኩላቸው፤ ኮሌጁ የግብርናውን ዘርፍ የሚደግፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ዛሬ ወደ ስራ የገባው የመስኖ አውታር የተለያዩ አትክልቶችን በማልማት ለመማር ማስተማር እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።

በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጁን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም