ቀጥታ፡

በክልሉ የተፋሰስ ልማት ውጤትን በማስቀጠል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)

ሾኔ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተፋሰስ ልማት ውጤትን አጠናክሮ በማስቀጠል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የክልሉ የ2018 የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሀዲያ ዞን ምስራቅ ባዳዋቾ ወረዳ አምቡርሴ አንጁሎ ቀበሌ በአንጁሎ ንዑስ ተፋሰስ ላይ ተጀምሯል።


 

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) መርሃ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የተፋሰስ ልማት ሥራ የአፈርን ለምነት በመጨመሩ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል፡፡

ዘንድሮው በበጋ ወራትም ሥራውን በተቀናጀ መንገድ በማስቀጠል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊና የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው ያለፉት ዓመታት የተፋሰስ ልማት ሥራዎች በክልል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዙ ነው።


 

በዚህም በ2015 የምርት ዘመን 142 ሚሊየን ኩንታል የነበረው ክልላዊ የምርት መጠን በ2017 ወደ 159 ሚሊየን ኩንታል በማደጉ ገበያም ማረጋጋት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል ብለዋል።

በተራቆቱ አካባቢዎች የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የእንስሳት መኖ ልማትን በማሳደግ የወተት ምርታማነትን በተመሳሳይ ዓመት ከነበረበት 321 ሚሊየን ሊትር ወደ 675 ሚሊየን ሊትር ማሳደጉን ተናግረዋል፡፡

ተግባሩን በማስቀጠል በዘንድሮ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማትም በ1ሺህ 294 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ ከ290 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም