ቀጥታ፡

ሀገር በቀል እውቀቶች ከዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት ጋር ተናበው እንዲተገበሩ የሚደረገው ጥረት መጠናክር አለበት

ሚዛን አማን፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ ሀገር በቀል እውቀቶች ከዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት ጋር ተናበው እንዲተገበሩ የሚደረገው ጥረት መጠናክር እንዳለበት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ተመራማሪና መምህር አማረ ፋንታው(ዶ/ር) እንዳሉት ሀገር በቀል እውቀቶችን ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለሥነ ምግባር ግንባታ ማዋል ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ነው። 

ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን ችግሮች በውይይት የሚፈቱበትን ማህበረሰባዊ እሴቶችና አሰባሳቢ ትርክቶችን ማጉላት ላይ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለተግባራዊነቱም ምሁራኑ ሀገር በቀል እውቀቶችን በማጥናት ከዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት ጋር ተናበው እንዲተገበሩ በሚደረገው ሂደት ይበልጥ አተኩረን መስራት ይገባናል ነው ያሉት።

በተለይም ሀገር በቀል የአስተዳደር እና የፍትሕ እውቀቶችን ወደ መደበኛው የመንግሥት አገልግሎት ለማስገባት የተጀመሩ ተግባራትን በሞያ መደገፍ እንደሚገባ ነው የጠቀሱት።


 

በዩኒቨርሲቲው የውጭ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህር ትዕዛዙ አቲሞ በበኩላቸው ከማኅበረሰብ ነባር ዕውቀቶች መካከል ወንጀልን የመመርመር ብልሀት፣ ትክክለኛ ፍርድ የመስጠት፣ ጠንክሮ የመሥራትና የመተጋገዝ ባህልን በዘመናዊ መንገድ በመቃኘት በመንግስት አገልግልት ለማካተት የተጀመሩ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።

 

ሀገር በቀል እውቀቶችን ለሀገር እድገትና የለውጥ ጉዞ ለማዋል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ የጎላ መሆኑንም አክለዋል።

 

በተደመረ አቅም የመሥራትና በእርቅና ይቅርታ ግጭቶችን የመፍታት ሀገረሰባዊ ባህሎችን ለትውልድ ለማስተላለፍ የተጀመሩ ተግባራት እንዲሳኩ ምሁራኑ በማማከርና በጥናትና ምርምር እያገዙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

 

ከዚህ ባለፈ የብሔር ብሔረሰቦች እሴቶችን ለማስተዋወቅና ለመሰነድ የሚደረጉ ጥረቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ ያላቸው ድርሻ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም