የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት ኢትዮጵያ መድን ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች በአራቱ አሸንፎ በስድስቱ ተሸንፌ በቀሪ አራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 12 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ጎሎችን አስተናግዷል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ መድን በ16 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ በ14 ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 17 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ወልዋሎ በ11 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ኢትዮጵያ መድን ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ማሸነፍ ወደ አሸናፊነት መንገድ ይመልሰዋል።
በሌላኛው መርሃ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ባህር ዳር ከተማ በሊጉ 14 ጨዋታዎች አድርጎ አራት ጊዜ ድል ሲቀናው በሶስቱ ተሸንፏል። በሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 11 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ19 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 14 ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ብቻ ያሸነፈው መቀሌ 70 እንደርታ በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል።
በ14ቱ ጨዋታዎች 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 19 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ12 ነጥብ 18ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ጨዋታው ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ መቀሌ 70 እንደርታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት እስከ ጥር 9 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ሲዳማ ቡና በ29 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አጥቂ አዲስ ግደይ ሰባት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በመምራት ላይ ይገኛል።