ቀጥታ፡

በምዕራብ ሀረርጌ ከ53 ሺህ በላይ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ ገብተዋል

ጭሮ፤ ጥር 7/2017 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ከ53 ሺህ በላይ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን የዞኑ ስራ ዕድል ፈጠራ ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

በፅህፈት ቤቱ የዕቅድ ዝግጅት ቡድን መሪ አቶ አሸብር ደበበ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ በበጀት አመቱ ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው።

ከታቀደው ውስጥም በስድስት ወራቱ በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በዶሮ እርባታና በግንባታ ስራዎች በ19 ሺህ 516 ማህበራት ወደስራ ገብተዋል ብለዋል።

በዞኑ  በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ  የገቡት ወጣቶች ከ53 ሺህ በላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ስራ ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል 2 ሺህ የሚሆኑት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ ሙያዎች የተመረቁ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የስራ እድል ፈጠራውን ውጤታማ ለማድረግም በገጠር አካባቢዎች ለመደበኛና መስኖ ልማት የሚውል ከ1 ሺህ 740 ሄክታር በላይ መሬት  መከፋፈሉን አመልክተዋል።

እንዲሁም በገጠርና ከተሞች 1 ሺህ 266 ሼዶች መተላለፋቸውንና የብድር አቅርቦት መመቻቸቱን አስታውቀዋል።

ወጣቶቹ ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ የሞያና የገበያ ትስስር እንዲሁም የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ስልጠና መሰጠቱን  ተናግረዋል።

ማህበራቱ ለምርታቸው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙም በተደረገው ቅንጅታዊ ተግባር ከ985 ሚሊዮን 973 ሺህ ብር በላይ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል ብለዋል።

በዞኑ በማህበር ተደራጅተው የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ቦኬ ወረዳ ቦኬ ጥቃ ከተማ በእንስሳት ማድለብ ስራ በማህበር ከተደራጁ ወጣቶች  መካከል  ጋሹ ኢብራሂም እንዳለው አራት ሆነው ለጀመሩት የከብት ማድለብ ስራ በተመቻቸላቸው  ግማሽ ሚሊዮን ብር ብድር ስራ እየሰሩ ናቸው።

የእንስሳት ማድለብ ስራውን ለማሳካትም የመስሪያ ቦታ፣ የብድር አገልግሎትና ሌሎች ድጋፎችን ከመንግስት ማግኘታቸውን ገልጿል።

ሌላው በዚሁ ወረዳ በከብት ማድልብ የተሰማራው ወጣት ሀብታሙ ገዛኸኝ በበኩሉ መንግስት የፈጠረለትን የስራ እድል ለማሳካት በትጋት መስራቱን ተናግሯል።

በቀጣይ ስራውን በማስፋት በወተት ላሞች እርባታ ላይ ለመሰማራት ተጨማሪ መስርያ ቦታ ከወረዳው መጠየቁን  ጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም