ሀገራዊ ምክክር ለጠንካራ ሀገር መንግስት ግንባታ መሠረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክር ለጠንካራ ሀገር መንግስት ግንባታ መሠረት ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክር ለዘላቂ ሰላም መስፈንና ለጠንካራ ሀገር መንግስት ግንባታ መሠረት መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ ገለፁ።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ትብብር “ሰላምን ማጽናት፤ ፀጋን ለማልማት” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ “ሀገራዊ ምክክር እና የሰላም ግንባታ” በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በጹሁፋቸውም በኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሀገራዊ ምክክር ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ቅቡልነት ያለው ጠንካራ ሥርዓተ-መንግስት ለመገንባት፣ የማያግባቡ ጉዳዮች ላይ በመመካከር ለመግባባትና የዲሞክራሲ ሥርዓትን ለማፅናት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ለዚህም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የችግሩን ጥልቀትና ባህሪ በመገንዘብ ከሌሎች ሀገራት በተሻለ መንገድና ሥነ ዘዴ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት፣ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከርና አዲስ ማህበራዊ ውልን በመፍጠር ልዩነቶችን ወደ ትብብር መቀየር ለዘላቂ ሰላም አይተኬ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክር ፈጣን መፍትሄ ሳይሆን፤ ረጅም ጊዜ የሚፈልግ ኢንቨስትመንት እንደሆነ ጠቁመው፤ ምክክሩ የሰላም ግንባታ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የሀገር ግንባታ መሠረት መሆኑን አስረድተዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን ይህን ታሪካዊ ዕድል በመጠቀም የወደፊት እጣ ፈንታቸውን እንዲወስኑና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።