ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል የሕክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማሳደግ ጤናማ እና አምራች ዜጋን የማፍራቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

ጅግጅጋ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፡- በሶማሌ ክልል የሕክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጋን የማፍራቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ገለፁ።

ካራማራ አጠቃላይ ሆስፒታል ያስገነባውን የእናቶች እና ህጻናት ማዕከል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃ መርሐ ግብሩ እንደገለፁት ሆስፒታሉ ያስገነባው የእናቶች እና ህጻናት ማዕከል ፈጣንና ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል።

የክልሉ መንግሥት ጤናማና አምራች ዜጋን ማፍራት የሚያስችሉ የጤና አገልግሎቶችን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁን ወቅት በክልሉ በተለይም ለእናቶች እና ህጻናት ጤና ትኩረት በመስጠት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ መንግስት የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ተቋማትን በሰው ሀይልና በግብዓት ማሟላት ላይ ትኩረት መስጠቱን አንስተዋል።


 

የካራማራ አጠቃላይ ሆስፒታል ያስገነባው የእናቶች እና ህጻናት ማዕከልም የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን እንደሚያሻሽል ጠቅሰዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሴ አህመድ በበኩላቸው በ2018 በጀት ዓመት በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎትን ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ የተመረቀው የካራማራ አጠቃላይ ሆስፒታል የእናቶች እና ህጻናት ማዕከል 100 አልጋዎች እንዳለው አስታውቀዋል።

ከካራማራ ሆስፒታል የእናቶችና ህጻናት ማዕከል በተጨማሪ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሼክ ሀሰን የበሬ ኮምፕሬሄንሲቭ ሆስፒታል የህጻናትና የአዋቂዎች የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ማዕከል፤ የሆስፒታሉ የላቦራቶሪ ማዕከል፤ የአስተዳድር ህንጻ እና የሶማሌ ክልል የላቦራቶሪ ማዕከልም ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም