ሀገራዊ ምክክሩ ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን በመቋጨት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ታሪካዊ እድል ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን በመቋጨት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ታሪካዊ እድል ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች
ሰመራ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በመቋጨት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ታሪካዊ እድል በመሆኑ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከዝግጅት እስከ አጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምእራፍ ድረስ በመዝለቅ ሂደቱን በስኬት ለመቋጨት በመስራት ላይ ይገኛል።
በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የቆዩ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በምክክር መፍታት የግድ መሆኑ ይታመናል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የቆዩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አካታችና ሁሉን አቀፍ የምክክር ሂደት ተጀምሮ በስኬት በመከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ሀገራዊ ምክክሩ እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በመቋጨት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ታሪካዊ እድል መሆኑን ገልጸዋል።
የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር ፓርቲ(አነግፓ) ሊቀ መንበር ሀንፈሬ አሊሚራህ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሳይፈቱ ዘመናትን የዘለቁ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ታሪካዊ እድል መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርቲያቸው ለሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳዎችን ቀደም ብሎ ማስረከቡን አስታውሰው በቀጣይነትም ለስኬታማነቱ የነቃ ተሳትፎ፣ እገዛ እና ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በየትኛውም አካባቢ ትጥቅ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላትም የጥፋት መንገዱን በመተው ለምክክር ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር(አርዱፍ) ምክትል ሊቀ መንበር መሐመድ አወል ወግሪስ በበኩላቸው፤ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን ለመቋጨትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሁነኛ መፈትሄ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሀገራችንን ችግሮች ወደ መድረክ በማምጣት ችግሮችን በምክክር ለመፍታት እድሉ በሁላችንም እጅ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት መሳካት የእያንዳንዱ ማህበረሰብ ተሳትፎና ሚና ወሳኝ መሆኑን አንስተው ችግሮቻችንን በራሳችን መንገድ ለመፍታት መዘጋጀት አለብን ብለዋል።