በክልሉ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ ገለፁ።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ትብብር የተዘጋጀው የፓናል ውይይት "ሰላምን ማጽናት፤ ፀጋን ለማልማት" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ሰላም ለማንኛውም ሀገራዊ እድገትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና አለው።
እንደ ሀገር አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ጠቅላላ ጉባኤውን መጥራት የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በክልሉ ያሉትን እምቅ የልማት ፀጋዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋልና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላምና መረጋጋት ቀዳሚው ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።
ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ፍላጎትን በኃይል የማስፈጸም አካሄድ ጊዜው ያለፈበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህ የፓናል ውይይት በክልሉ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የልማት ስራዎች ምቹ በሆነ ሁኔታ ለማካሄድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ያግዛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ በአማራ ክልል ሰፊ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የልማት ፀጋዎች እንዳሉ ተናግረው፤ እነዚህን ፀጋዎች በአግባቡ ለመጠቀም ሰላምን ማፅናት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢዜአ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ለሰላም ግንባታ የሚረዱ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የፓናል ውይይትም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አባይ መንግስቴ ሰላምን በማጽናት ረገድ የሚዲያ ተቋማት እና የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህ መድረክ በክልሉ ሰላምን አፅንቶ ፀጋን ለማልማት የሚደረገውን ጉዞ ለማፍጠን ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል።