ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ተግባር ተኮር ሥልጠና በመስጠት ለተመራቂዎች የሥራ አማራጮችን ለማስፋት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ተግባር ተኮር ሥልጠና በመስጠት ለተመራቂዎች የሥራ አማራጮችን ለማስፋት እየሰራ ነው
ሮቤ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ተግባር ተኮር ሥልጠና በመስጠት ለተመራቂዎች የሥራ አማራጮችን የማስፋት ስራ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርሀነመስቀል ጠና(ዶ/ር) እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ማፍራት ዓላማ አድርጎ እየሰራ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በመደበኛነት ከሚያስተምረው ትምህርት በተጨማሪ ተመራቂዎች በሥራ ዓለም ውጤታማ እንዲሆኑ በሥራ ፈጠራና በንግድ ክህሎት ተግባር ተኮር ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት 250 ለሚሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች በሥራ ፈጠራ ጥበብ፣ በቢዝነሥ ዕቅድ አዘገጃጀትና አካባቢያዊ አማራጮችንና ተግዳሮቶችን መለየት ላይ ያተኮሩ ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን አስታውሰዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፣ ተመራቂዎችም በሥራ ፈጠራ ክህሎት ላይ የወሰዱትን ሥልጠና ተግባራዊ በማድረግ ከቅጥር ጠባቂነት አሥተሳሰብ በመላቀቅ የሥራ ፈጣሪነት ሥሜትን ማጎልበት እንዳለባቸው መክረዋል።
ስልጠናውን የወሰዱ ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው ሥልጠናው በቅጥር ላይ ብቻ ተገድቦ የነበረውን እሳቤ በማስፋት አማራጮችን እንዲፈትሹ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተመራቂ ሊና ወዩ በሰጠችው አስተያየት፤ ከዚህ በፊት በተለያዩ ተቋማት ተቀጥሮ መስራትን እንደ ትልቅ ግብ ይዛ እንደነበር አስታውሳለች።
ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ ትምህርት በተጓዳኝ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሰጣቸው ተግባር ተኮር ሥልጠና ከተቀጣሪነት አስተሳሰብ በመውጣት በአካባቢያቸው የሚገኙ አማራጮችን ለመፈተሽ ስንቅ ይሆናል ብላለች።
ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የገበየውን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የራሱን ሥራ ለመፍጠር ትልቅ እድል እንዳለው የገለጸው ደግሞ ተማሪ አብዱሮ ክኒሶ ነው።
በተለይም በቢዝነስ እቅድ አዘገጃጀት ላይ የቀሰሙት ተግባር ተኮር እወቀት በሥራ ዓለም ውጤታማ መሆን የሚያሥችል መሆኑን አክሏል።
ሌላዋ የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪ ኤደን በጋሻው በበኩሏ የተሰጣቸው ሥልጠና ሥራ ለመፍጠር የሥነ-ልቦና ዝግጅት ለማድረግ አቅም እንደፈጠላት ተናግራለች።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ በንድፈ ሀሳብ ካገኘችው ዕውቀት በተጓዳኝ በየአካባቢው የሚገኙ የሥራ ዘርፎችን በመፈተሽ በትንሽ የመነሻ ካፒታል ወደ ሥራ መግባት እንደሚቻል እውቀት መገብየቷን አክላለች።
ሌላው የዩኒቨርሲቲው ተመራቂ ተማሪ አቤል ተሰማ፤ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀትና ክህሎት በዙሪያው ካሉ መልካም አጋጣሚዎች ጋር በማቀናጀትና ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት ወደ ሥራ መግባት የሚያሥችል የሥነ-ልቦና ዝግጅት ማድረጉንም ገልጿል።
ሥልጠናው በቅጥር ላይ ብቻ ተገድቦ የነበረውን እሳቤያቸንን በማስፋት ሌሎች የሥራ አማራጮችን እንድንፈትሽ ዕድል የፈጠረ ነው ያለው ደግሞ የጋዜጠኝነትና የስነተግባቦት ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተማሪው ደስታ ደበለ ነው።
ተግባር ተኮር ሥልጠናው በኢንተርፕርነርሺፕ እሳቤ፣ የንድፍ አዘጋጀጀትና የገበያ ጥናት ላይ ተጨማሪ ዕውቀት እንድናገኝና የስነልቦና ዝግጅት ጭምር እንድናደርግ አግዞናል ብለዋል።