ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ሰላምን በማፅናት ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፤ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት በመፍታትና ሰላምን በማፅናት ሁሉን አቀፍ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ትብብር "ሰላምን ማጽናት፤ ፀጋን ለማልማት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የፓናል ውይይት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ሰላም የልማትና የዕድገት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ያሉትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች፣ የግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ኢንዱስትሪ እምቅ አቅሞችን በአግባቡ ለማልማትና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው ብለዋል።

መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ችግሮችን በዘላቂነት በውይይት ለመፍታት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም 28 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም አማራጭ በመቀበል የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።


 

የታጣቂ ቡድን አመራሮች ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣታቸው የፖለቲካ ጥያቄዎችን በኃይል ሳይሆን በውይይትና በዲሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት ብቸኛውና አስተማማኙ መንገድ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በክልሉ ያለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና ወደ መደበኛ የልማት ሥራዎች ለመመለስ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት "ሰላምን ማጽናት፤ ፀጋን ለማልማት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ያለው መድረክ በክልሉ ሰላምን በማፅናት ልማትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ላለው ጥረት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም