ቀጥታ፡

በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተፈጠረው ምቹ መደላድል በቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ከፍ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን እየሳበ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦መንግስት በኢንቨስትመንት ዘርፍ የፈጠረው ምቹ መደላድል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙና በቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ከፍ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ አቅም እየፈጠረ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በትላንትናው እለት የሁዋጂያን ዓለም አቀፍ ቀላል ኢንዱስትሪ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።


 

ጉብኝቱ በዋናነት በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን የስራ እንቅስቃሴ በመፈተሽና በመንግስት በኩል ሊደረግላቸው የሚገቡ እገዛዎችን በመለየት በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የውጭ ባለሀብቶች በተወሰኑ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ይሰማሩ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ዘመኑን የዋጁና ቴክኖሎጂን መሰረት ባደረጉ  ኢንቨስትመንቶች ላይ የመሰማራት ፍላጎታቸው እያደገ መጥቷል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ፣ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት መሻሻሉ፣ የሰለጠነ የሰው ሀይል በዘርፉ ላይ መሰማራቱ ለፍላጎቱ ማደግ መሰረት መጣሉን አንስተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከኢንቨስትመንት የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ በቅርቡ በሀዋሳ  ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ የጀመረው ቶዮ ሶላር ፋብሪካ በስድስት ወራት ብቻ 55 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ  ማስገኘቱን በአብነት አንስተዋል፡፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ መልካም እድል ይዞ መምጣቱንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ስትራቴጂው ኢንዱስትሪዎች ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ፣ የምርት ጥራትን እንዲያረጋግጡ እና በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት እና ተደራሽነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያሸጋግሩ ያስችላል ብለዋል።

ፋብሪካዎቹ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ለዘርፉ ተዋናዮች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አመላክተዋል።


 

የሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ምክትል ፕሬዝዳንት አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ሶላር ሴል የሚያመርት ኩባንያ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

ኩባንያው ስራውን በሁለት ምዕራፍ እንደሚያከናውን ጠቅሰው በመጀመሪያው ምዕራፍ የሶላር ሴሎችን በማምረትና ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ 100 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት  አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም