ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከለውጡ ጋር በመጣ የቱሪዝም ንጋት እየደመቀች እና እየለማች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከለውጡ ጋር በመጣ የቱሪዝም ንጋት እየደመቀች እና እየለማች ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የኢትየጵያ የዘመናት የቱሪዝም መዝገብ ሲገለጥ የሚነበበው በልኩ ያልደመቀ መልክዓ ተፈጥሮ፣ በወጉ ያልተገለጠ የታሪክ ግርማ፣ ሌማት ሆኖ ያልቀረበ ሃብት እና ውበት ነው ብለዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቱሪዝም ዘርፍ የመጣው ለውጥ ይህንን ሁሉ የዘመናት ችግር ከመሰረቱ የናደ አዲስ የቱሪዝም ልማት አምዶችን ያቆመ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የለውጡ መንግስት ቱሪዝምን እንደ አንድ የኢኮኖሚ መሰረት በመውሰድ በትጋት ሰርቷል፡፡ አሁን የድካሙ ፍሬ እየተሰበሰበ፣ የሃገራዊ ጥረቱ አዝመራ እየታጨደ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም ድንቅ ውጤት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዘርፉን በጠራ ራዕይ ተመልክተው፣ ለቱሪዝም የነበረውን እሳቤ ከማስተካከል ጀምሮ ሃገር እና ትውልድን ማዕከል ያደረገ አመራር በመስጠት የሰሩት ስራ የስኬቱ በር ከፋች ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ዛሬ በቱሪዝም ዘርፍ እያየን ያለነው ስኬት ሁሉ እንደ ቀን ንጋት የሚቆጠር የስኬት አሃዱ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም