ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለትውልዱ የምትመች ጠንካራ ሀገርን በጋራ እንገነባለን

ሽረ እንዳስላሰ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለትውልዱ የምትመች ጠንካራ ሀገርን በጋራ እንገነባለን ሲሉ በትግራይ ክልል የሽረ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

በሀገራዊ ምክክር ሂደት በንቃት በመሳተፍ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም የከተማዋ ወጣቶች አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በብሄራዊ ደረጃ ሁሉን አቀፍ፣ አካታችና አሳታፊ ምክክር እየተካደ ይገኛል።

በእስካሁኑ ሂደትም በ11 ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ ተደርጎ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ስኬታማ በሆነ መልኩ ማከናወን ተችሏል።

የምክክሩን የመጨረሻ ግብ ለማሳካት የኮሚሽኑ ሁሉን አቀፍ ጥረት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን የትግራይ ክልል ህዝብም እንደ ሌሎች ክልል ህዝቦች የሚመክርበትን እድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

ምክክሩን በሚመለከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የሽረ እንዳስላሴ ወጣቶች በሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለትውልዱ የምትመች ጠንካራ ሀገር በጋራ መገንባት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህ ሂደት መሳካት የኮሚሽኑ ጥረት እንዳለ ሆኖ አጠቃላይ የህዝቡ ትብብርና ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ለተግባራዊነቱ ወጣቶቹ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ከከተማዋ ወጣቶች መካከል ኤፍሬም ሰለሞን፤ በምክክር የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በተለይም እኛ ወጣቶች የላቀ ሚና ይጠበቅብናል ብሏል።

የወጣቶችና የቀጣዩ ትውልድ ጭምር እጣ ፈንታ የሚወሰነው ዛሬ ላይ ሰላም የሰፈነባት፣ የተረጋጋችና ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የሚከናወኑባት ሀገር መገንባት ሲቻል በመሆኑ ለዚህ መትጋት ይገባናል ነው ያለው።

ሌላኛው ወጣት አታክልቲ አማረ በበኩሉ፤ የምክክር ሂደቱ እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታት ታሪካዊ እድል በመሆኑ የትግራይ ክልል ህዝብም እንደ ሌሎች ክልል ህዝቦች ሁሉ የሚመክርበት እድል ይፈጠርለት ዘንድ ይሻል ብሏል።

በመሆኑም ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት ዛሬ ላይ በጋራ መክረን ችግሮቻችንን መፍታት የሁላችንም ግዴታ ነው ሲልም ተናግሯል።

የልዩነትና የአለመግባባት ምክንያቶችን በምክክር ለመቋጨት የምክክር ሂደቱ ለዚህ ትውልድ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን የተናገረችው ደግሞ ወጣት ንግስተይ ሸዊት ነች።

ለምክክሩ ስኬታማነት የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አንስታ በተለይም ወጣቶች ትልቅ ሃላፊነት አለብን በማለት ለምክክር ኮሚሽኑ ሁለንተናዊ ጥረት እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም