ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከት መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አከባበር በስኬት እንዲከናወን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ክልሎችና ተቋማት የእውቅናና መርሃ ግብር እያካሄደ ነው።

አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በተለይ ከለውጡ ወዲህ እውነተኛ የፌደራል ስርዓት መተግበሩን በሚያረጋግጥ መልኩ ሲከበር ቆይቷል።


 

በዓሉ የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር በማድረግ በኩል ዓይነተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ህብረ ብሄራዊ አንድነት እየጎለበተ እንዲመጣ ማስቻሉንም አብራርተዋል።

ዘንድሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ የተከበረው የብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን በተበሰረበት፣ በኢትዮጵያውያን የጋራ ርብርብ እውን የሆነው የህዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበት ወቅት መሆኑ ልዩ ገጽታ አላብሶታል ብለዋል።

በዓሉ በሁሉም መመዘኛዎች ስኬታማ እንደነበር አስታውሰው ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ መገናኛ ብዙሃን፣ ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች እንዲሁም የክልል አፈ ጉባኤዎች ምስጋና አቅርበዋል።


 

በመርሃ ግብሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ፣ የክልል አፈ ጉባኤዎችን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም