በጉጂ ዞን በመኸር አዝመራ ከለማው ሰብል ከ8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በጉጂ ዞን በመኸር አዝመራ ከለማው ሰብል ከ8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል
አዶላ ፤ጥር 7/ 2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በመኸር አዝመራ ከለማው ሰብል እስካሁን ድረስ ከ8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በጽህፈት ቤቱ የእቅድና ግምገማ ቡድን መሪ አቶ ጃለታ ተሰማ በዞኑ ባለፈው መኸር ከ498 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን አስታውሰዋል።
ከልማቱም ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ የሰብል እንክብካቤ ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።
የደረሰን ሰብል በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሰው `ኃይል በመታገዝ በተከናወነው እንቅስቃሴ 8 ሚሊዮን 460 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።
ከተሰበሰው ሰብል መካከል ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ ቦለቄና ሰሊጥ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የተሰበሰበው ሰብል ከዓምና ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለው ገልጸው ብልጫው የመጣው የተሻሻለ የግብርና አሰራር ጥቅም ላይ በመዋሉ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ከ347 ሺህ ሄክታር በላይ ሰፊ የእርሻ ማሳዎችን በትራክተር በመታገዝ በኩታ ገጠም እና በመስመር መዝራት በመቻሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የምርት ማሳደጊያ ግብዓት አቅርቦት በአግባቡ በመቅረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ አናሶራ ወረዳ የራያ ቦዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሂርባዬ በሪሶ፣ በመኸር አዝመራው ያለሙትን ስንዴ፣ ገብስና ቦለቄ ምርት መሰብሰባቸውን ገልጸዋል።
ሰብሉ ከተነሳበት ቦታ ላይም በበልግ እርሻ ቶሎ የሚደርስ ሰብሎችን በኩታ ገጠም ለማልማት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
የዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገዳ ዴከማ፣ በመኸር አዝመራው ስንዴ፣ ጤፍና ባቄላ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም በማልማት የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ እየተደረገ ያለው የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ድጋፍና ክትትልም የምርት ብክነትን ማስቀረቱን ገልጸዋል።