ፌዴራል ፖሊስ የሻዕቢያ መንግሥት በፋኖ ስም የሚነግዱ ሽፍቶችን ለማስታጠቅ በስውር የላከውን ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር አዋለ - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴራል ፖሊስ የሻዕቢያ መንግሥት በፋኖ ስም የሚነግዱ ሽፍቶችን ለማስታጠቅ በስውር የላከውን ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር አዋለ
አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሻዕቢያ መንግሥት በፋኖ ስም የሚነግዱ ሽፍቶችን ለማስታጠቅ በስውር የላከውን ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሻዕቢያ መንግሥት ከኢትዮጵያ የውስጥ ባንዳዎች እና ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ በፋኖ ስም የሚነግዱ ሽፍቶችን ለማስታጠቅ በስውር የላከውን ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶችን ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በወልዲያ የፍተሻ ጣቢያ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጿል።
እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ጥይቶቹ በሻዕቢያ መንግሥት እንደተላኩ እና ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል መቀሌ ላይ ተቀብሎ ወደ አማራ ክልል ሸዋሮቢት በማስገባት በፋኖ ስም ለሚነግዱ ሽፍቶች ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ተረጋግጧል።
ለሻዕቢያ መንግሥት ድልድይ ሆኖ እየሠራ ያለው ፅንፈኛው የህወሃት ቡድን በፋኖ ስም የሚነግዱ ሽፍቶችን በማስታጠቅ የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ አቅዶ ከኤርትራ በመቀሌ በኩል በስውር የላከውን 41 ሺህ 999 የክላሽ ጥይት፣ 14ሺህ የብሬን ጥይት እና 800 የድሽቃ ጥይት በአጠቃላይ 56 ሺህ 799 ጥይቶችን ወደ ሸዋሮቢት ለማስገባት ሲያጓጉዙ በወልዲያ የፍተሻ ጣቢያ ተይዘዋል።
በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አ.አ B94744 የጭነት አይሱዙ ተሽከርካሪ ከሲሚንቶና ከብሎኬት ጋር አመሳስሎ በመጫን በአማራ ክልል ወልዲያ ከተማ አድርገው ሲያጓጉዙ በወልዲያ የፍተሻ ጣቢያ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጠንካራ ክትትልና ፍተሻ እንደተያዙ ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።
ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገልጿል።
ባዳዎች እና ባንዳዎች ተቀናጅተው የሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስ ፣ሀገራችን እያካሄደች ያለችውን ልማትና ዕድገት ለማደናቀፍ በተለያዩ ጊዜ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወቃል።
አሁን ላይም እነዚህ የጠላት ኃይሎች በሀገራችን ላይ አደጋ ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው የፀጥታ ኃይሉ የጀመረውን ኦፕሬሽን አጠናከሮ እንደሚቀጥል እየገለፀ ኅብረተሰቡም ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር የተለመደውን ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።