ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላምን ጥሪ ተቀብለው እንዲመጡ ህብረተሰቡ ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገ ነው - ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ

ደብረብርሃን፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላምን ጥሪ ተቀብለው እንዲመጡ በማድረግ ሂደት ህብረተሰቡ ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ ተናገሩ።

በሰሜን ሸዋ ዞንና በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ የቀድሞ ታጣቂዎች በደብረ ብርሃን ስልጠና ማዕከል የተሃድሶ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።


 

ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ፤ በደብረ ብርሃን የተሃድሶ ስልጠና ማዕከል በስልጠና ላይ ለሚገኙ ለቀድሞ ታጣቂዎች ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ገለጻ አድርገዋል።

ሌተናል ጀነራል ሹማ፤ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክትም የመንግስትን የሰላም አማራጭ በመቀበል ወደ ሰላም እየመጡ ያሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እንዲመጡ በማድረግ ሂደት ህብረተሰቡ ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን አስታውሰው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

በተሳሳተ መንገድ አሁንም በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች መንግስት ለሰላም የሰጠውን እድል እንዲጠቀሙበት አሳስበው ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደጀኔ ልመንህ፤ የሰላም አማራጭን በመቀበል ወደ ተሃድሶ ስልጠና የገባችሁ ሁሉ በቀጣይ በምትፈልጉት የልማት ዘርፍ እንድትሰማሩ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በክልሉ አሁን ላይ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩን አንስተው የዘላቂ ሰላም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በተሃድሶ ስልጠና ላይ የሚገኙ የቀድሞ ታጣቂዎች በበኩላቸው ከስልጠናው በኋላ ወደ ሰላማዊ ህይወት በመመለስ የልማት አርበኛ እና የሰላም አምባሳደር ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ከቀድሞ ታጣቂዎቹ መካከል አስቻለው ተፈሪ፣ አበበ ወርቁ እና አስቻለው ተሻለ፤ በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ በመግባት ለህዝቡ እንግልትና ስቃይ ምክንያት መሆናቸውን አስታውሰው በመፀፀት ህዝብን ለመካስ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ሌሎች በጫካ የሚገኙ ወገኖችም የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከጥፋት መንገድ ወጥተው እንዲመጡ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም