ቀጥታ፡

መንግስት ያመቻቸልን የሥራ ዕድል እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት የተደረገልን ድጋፍ በሀገር ሰርተን መለወጥና ለሌሎች እንድንተርፍ አስችሎናል

ሆሳዕና፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት ያመቻቸላቸው የሥራ ዕድል እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት የተደረገላቸው ድጋፍ በሀገር ሰርተው መለወጥ እና ለሌሎች እንዲተርፉ እንዳስቻላቸው በሆሳዕና ከተማ ከስደት ተመላሾችና ዳያስፖራዎች ገለጹ፡፡


 

በሰው የመነገድ ወንጀልን መከላከል እና በዳያስፖራ ተሳትፎ ላይ አተኩሮ በተዘጋጀ መድረክ የተገኙ ተሳታፊዎች በሆሳዕና ከተማ ከስደት ተመላሾችና በዳያስፖራዎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት ከስደት ተመላሶቹና በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ዳያስፖራዎች በመንግስት የተመቻቸላቸውን ዕድል በመጠቀም በሀገር ሰርቶ መለወጥና ለሌሎችም መትረፍ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡


 

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የሆሳዕና ከተማ ነዋሪው ተስፋዬ ተፈራ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ጉዞ ሳይሳካ ቀርቶ በኬንያ ለአምስት ዓመታት በእስር ቤት ማሳለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከእስር ቆይታ በኋላ በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ጠቁመው፣ በመንግስት በተመቻቸላቸው የሥራ ዕድል ተጠቅመው ጠንክረው በመስራት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከሰባት ዓመት በፊት ከመንግስት በተመቻቸላቸው 70ሺህ ብር ብድር እና የ3 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት ተጠቅመው በጀመሩት ጥምር ግብርና ሥራ ውጤታማ በመሆን አሁን ላይ ካፒታላቸውን ወደ 70 ሚሊየን ብር ማሳደጋቸውን ገልጸዋል።

በቀን 650 ሊትር ወተት ለገበያ እንደሚያቀርቡ ጠቅሰውም በስራቸው ለ35 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡



ከህገ ወጥ ስደት መልስ መንግስት ባመቻቸላቸው የሥራ ዕድል ተጠቅመው በተሰማሩበት የዱቄት ፋብሪካ ሥራ ውጤታማ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ታምራት ደበሮና ናቸው።

ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንደተሰማሩ ገልጸው፣ በስራቸው ስኬታማ እንዲሆኑ መንግስት የገንዘብ ብድር፣ የመስሪያ ቦታና የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸው 95 ሚሊየን መድረሱን ጠቁመው፣ በሀገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል እሳቸው ማሳያ እንደሚሆኑን  በስራቸውም ለ64 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

 

በህጋዊ መንገድ ተጉዘው በውጭ ሀገር ያፈሩትን ሃብት በሃገራቸው ኢንቨስት ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ በሆሳዕና ከተማ የሆቴል ባለቤት የሆኑት ታረቀኝ ዘለቁ ናቸው።

580 ሚሊየን ብር ኢንቨስት በማድረግ ሆቴል መገንባታቸውን ገልጸው፣ መንግስት ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የፕሮሞሽን ፍቃድ መረጃና ዳያስፖራ ዳይሬክተር ተወካይ ያለው አድነው በበኩላቸው ከስደት ተመላሾችና ዳያስፖራዎች በልማት ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት።

በሀገር ውስጥ ሰርቶ ለመለወጥ ቁርጠኛ ለሆኑ የመስሪያ ቦታና የተለያዩ ድጋፎች እንደሚመቻቹ ጠቅሰው ይህን በመጠቀምም በርካቶች ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል ብለዋል።



የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ አገልግሎቱ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ለኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ ለውጤታማነታቸው እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከስደት ተመላሾችም ሆነ የዳያስፖራ አባላት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ በመሳተፍ እያስመዘገቡ ካሉት ለውጥ በተጨማሪ ለማህበረሰቡ አርአያ በመሆን የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን በመስክ ምልከታው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ዳያስፖራው በኢንቨስትመንትና በሀገር ልማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም