ቀጥታ፡

በዞኑ ሰላም የማጽናት ስራው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ አድርጓል

መተማ፤ ጥር 6/2018 (ኢዜአ):- በምዕራብ ጎንደር ዞን ማህበረሰቡን በማሳተፍ በተከናወነ ሰላም የማጽናት ስራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ ማድረጉን  የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። 

አስተዳደሩ በግማሽ ዓመቱ የተከናወኑ የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ዛሬ በመተማ ከተማ አካሂዷል። 

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በዞኑ ማህበረሰቡን በማሳተፍ የአካባቢውን ሰላም ለማፅናት በተደረገ  ሁሉን አቀፍ ጥረት አበረታች ውጤት ተገኝቷል።

በዚህም  ትራንስፖርትን ጨምሮ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  እንቅስቃሴዎች  እንዲሳለጡ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።


 

የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብትና ፀጋ በመለየትና በማልማት የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት በበለጠ ለማረጋገጥ መሰረት መጣሉንም ጠቁመዋል።

በዘርፉ ለተገኘው ስኬት የፀጥታ ሃይሎች ህብረተሰቡን በማሳተፍ ያከናወኑት ተግባር ወሳኝ ድርሻ እንደነበረው አመልክተዋል። 

በብልፅግና ፓርቲ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለው ማሩ በበኩላቸው፤ የተለያዩ የህዝብ መድረኮችን በማካሄድ ህዝቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል። 

ማህበረሰቡን በማሳተፍ የተገኘውን ሰላም አፅንቶ ለማዝለቅ የተጀመረውን ቅንጅታዊ አሰራርና ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመላክተዋል። 

በዞኑ ያለውን ሰላም በመጠቀም የበጋ መስኖና የተፋሰስ ልማት ስራዎችን በአግባቡ ለመደገፍና ለማከናወን ተችሏል ያሉት ደግሞ  የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ጤናው ፋንታሁን ናቸው። 

በዞኑ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እየለማ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል። 

በውይይት መድረኩ ላይ የዞኑ አመራር አካላት፣ የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም