ቀጥታ፡

የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር ለአካባቢያችን ልማትና ዕድገት ለማዋል እንሰራለን

ሚዛን አማን፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር ለአካባቢያቸው ልማትና ዕድገት ለማዋል እንደሚሰሩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የ"ቢስት ባር" በዓል ታዳሚዎች ገለጹ።

የቤንች ዘመን መለወጫ በዓል "ቢስት ባር" በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ታዳሚዎች መካከል ከካፋ ዞን የመጣው አርቲስት ሻምበል አሥራት እንዳለው በክልሉ በአብሮነት የሚከበሩ በዓላት ለህብረተሰቡ አንድነት መጠናከር የጎላ ሚና እየተጫወቱ ነው።

በክልሉ ያሉ የባህልና የተፈጥሮ ሀብቶች ለኢኮኖሚ ጥቅም ማዋል የሚቻለው አንድነትን እንደ ኃይል ተጠቅመን ስንሰራ ነው ያለው አርቲስቱ፣ ለክልሉ የልማት ጉዞ ስኬታማነት የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ገልጿል።

ለዚህም ለህዝቦች የአብሮነትና የመቻቻል ባህል መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁሞ፣ አንድነትን በማጎልበት የክልሉን ልማት ለማፋጠን እንደሚሰራ ገልጿል። 


 

ከምዕራብ ኦሞ ዞን የተገኙት ትዕዛዙ ካሳሁን በበኩላቸው በዓሉ ተደብቀው የቆዩ ባህላዊ ዕሴቶችን በአደባባይ ለማውጣት ከማስቻሉ ባለፈ የህብረተሰቡን አንድነትና ትስስር የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

በበዓሉ ለመታደም ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት በጋራ ተሰባስበው ማክበራቸው ወንድማማችነትንና የእርስ በርስ ትስስራቸውን ለማጠናከር እያገዛቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

ባህላዊ እሴቶቻችን ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነትን የሚያጎለብቱ ናቸው ያሉት ደግሞ ከቤንች ሸኮ ዞን በዓሉን የታደሙት አለማየሁ ፎርጫብ ናቸው።

በዓሉን ከሩቅም ከቅርብም ከመጡት ጋር በተደመረ ማንነት በጋራ ማክበራችን ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል። 

አንድነታችንን የሚያጠናክሩ በዓላት ሰላማችንን ለማይፈልጉ ጠላቶች በር እየዘጋ በመሆኑ የበዓላቱ ትውፊቶች ጠብቆ ለትውልድ ለማቆየት እንሰራለን ሲሉም አክለዋል።

የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ጥሩዬ ከበደ አንድነትና ፍቅርን የሚያጠናክሩ የአባቶቻችንን ባህላዊ ዕሴቶች በመጠበቅ ለልማት ለማዋል በሚሰሩ ሥራዎች የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ለአካባቢያቸው ልማትና ሰላም መጠናከር ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ በተጨማሪ የአብሮነትና የመቻቻል ባህል እየተጠናከረ እንዲመጣ በሚችሉት ሁሉ ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም