በድሬዳዋ የትምህርት ፍትሃዊነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ውጤታማ ናቸው - ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ የትምህርት ፍትሃዊነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ውጤታማ ናቸው - ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬዳዋ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ የትምህርት ፍትሃዊነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ዲጂታል የትምህርት ስርዓትን ለማዘመን የሚያግዝ የመምህራን መረጃ አስተዳደር ዲጂታል መተግበሪያ ዛሬ ወደ ስራ አስገብቷል።
የዲጂታል መተግበሪያውን ስራ ያስጀመሩት ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንዳሉት፤ በአስተዳደሩ የትምህርት ፍትሃዊነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ውጤታማ ናቸው።
በተለይም የትምህርት አሰጣጥን በዲጂታል አሰራር መተግበር፣ በትምህርት ዘርፉ ያሉ ስራዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመረጃ አያያዙን ለማዘመን መሰራቱን ጠቅሰዋል።
በዛሬው ዕለት ተመርቆ ወደ አገልግሎት የገባው ዲጂታል የትምህርት ቤቶችና የመምህራን መረጃ አስተዳደር ስርዓት የመምህራን ቅጥር፣ ዝውውር፣ ዕድገት እና ተያያዥ ጉዳዮችን በግልፅነትና ተጠያቂነት በመተግበር በዘርፉ የላቀ ውጤት ማምጣት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ቢሮው ተግባራዊ ያደረጋቸው ስራዎች በአስተዳደሩም ሆነ በብሔራዊ ደረጃ በሚሰጡ ፈተናዎች የላቀ ውጤት ማምጣት እንደሚያስችሉም ጠቅሰዋል።
የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሱልጣን አልዪ በበኩላቸው በአስተዳደሩ ዲጂታል አሰራሮችን በመተግበር የትምህርት ስራና አሰራርን ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በአስተዳደሩ ለ42 ዓመታት የተሰጡ የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል የፈተና ውጤት ማጠናቀሪያ የዳታ ቤዝ ስርዓት መተግበሩን አንስተው፤ የእነዚህን ክፍሎች ተማሪዎች በበይነመረብ መመዝገብ፣ ፈተናን ማረም፣ ውጤት በማሳወቅ በኩል በዲጂታል ፈጣን አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ዛሬ ወደ አገልግሎት የገባው ዲጂታል አሰራርም መረጃዎችን በማደራጀት ቀልጣፋ አገልግሎትና ውሳኔዎችን በመስጠት የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን ማሳደግ ያስችላል ነው ያሉት።
በስነስርዓቱ ላይ የቀድሞ አንጋፋና አርአያ ስራ የሰሩ መምህራን የህይወት ተሞክሮ የተገለፀበትና ለቀጣዩ ትውልድ ተሞክሮ የሚሰጥ መፅሐፍም ተመርቋል።