የግብርና ዘርፉን በማዘመን የገጠር ሽግግርን ማሳካት የሚያስችል አቅምና ሥርዓት እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ዘርፉን በማዘመን የገጠር ሽግግርን ማሳካት የሚያስችል አቅምና ሥርዓት እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን በማዘመን የገጠር ሽግግርን ማሳካት የሚያስችል አቅምና ሥርዓት እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች የኢንስቲትዩቱን 15ኛ ዓመት ምስረታ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) በመግለጫቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያን የግብርና የዕድገትና የትራንሰፎርሜሽን ጉዞን ለማፋጠን የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
የዘርፉን ችግሮች በጥናት መለየትና የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ፣ ውጤታማ ሙከራዎች ማስፋፋት፣ በፖሊሲ ጥናትና በአሰራር ስርዓት የትግበራ ድጋፍ የማድረግና ቅንጅትና ትስስር የመፍጠር ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት ግብርናውን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግርና የገጠር ሽግግርን በተሟላ መልኩ ለማሳካት መሰረት የሚሆን አቅምና ሥርዓት እየገነባ መምጣቱን ተናግረዋል።
የግብርና እና ገጠር ሽግግርን በመፍጠር ሀገርን የማበልጸግና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ማሳካት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ በመቅረጽ የጎላ አበርክቶ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ግብ የግብርና ሽግግር መፍጠር መሆኑን ጠቁመው፤ የአገልግሎት እና ኢንዱስትሪውን ሚና ማላቅ የሚያስችል ጥናት እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የገጠር ሽግግርን ለመፍጠር የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ማሳደግና የተቋማትን አቅም መገንባት ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የገጠር ሽግግሩን እውን ለማድረግ በክልሎች ያለውን አስቻይ ሁኔታ፣ አቅምና ችግሮችን በጥናት በመለየት እንዴት ሽግግር ማድረግ እንዳለባቸው አቅም እንገነባለን ነው ያሉት።
የግብርና ሽግግር ወደ ገጠር ሽግግር አደገ የሚባለው አርሶ አደሩ ከሚያመርተው ውስጥ 75 በመቶ ትርፍ ምርት ለገበያ ማቅረብ ሲችል መሆኑንም ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በግብርና ዘርፍ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ዲጂታል ኢኖቬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ግሩም ከተማ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአርሶ አደሮች ፕሮፋይል ከክልል ጀምሮ በተዋረድ በፋይዳ መታወቂያ አማካኝነት በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር አርሶ አደሮች የግብርና መረጃዎችን በቀላሉ የሚያገኙበት በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ እና 8028 አጭርና ነጻ የጥሪ መስመር ስራ ላይ መዋሉን ተናግረዋል።
በዚህም ከሰባት ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች መመዝገባቸውንና ከ67 ሚሊየን በላይ ጥሪዎችን ከአርሶ አደሮችና የልማት ሰራተኞች ተቀብሎ ማስተናገድ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ብሩክታዊት እጅጉ(ዶ/ር)፥ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት 15 ዓመታት ከ400 በላይ ጥናቶችን በማከናወን 80 በመቶውን ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቀዋል።
በዚህም ዓለም አቀፍ ጥናትን መሰረት ያደረጉ ከ70 በላይ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በሰባት ክልሎች መተግበሩን ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም ምርታማነትንና ገቢያቸውን ማሳደግ የሚችሉበት ፕሮጀክት መኖሩንም ነው የተናገሩት።
ግብርናን አዋጭና ሳቢ በማድረግ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ከ600 ሺህ በላይ ወጣቶችን ማሳተፍ የሚያስችል የአደይ ፕሮግራም በመተግበር ላይ ነው ብለዋል።