ቀጥታ፡

በደሴ ከተማ የጥምቀት በአልን አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር በቅንጅት እየተሰራ ነው

ደሴ፤ ጥር 6/2018 (ኢዜአ)- በደሴ ከተማ  የጥምቀት  በአልን  አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ በድምቀት ለማክበር  በቅንጅት  እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።  

የደሴ ከተማ አስተዳደር  የጥምቀትና ሌሎች በጥር ወር የሚከበሩ በአላትን  በስኬት ለማክበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ የጥር ወር ጥምቀትን ጨምሮ ሌሎች  በአደባባይና በጎዳና ላይ የሚከበሩ  በዓላት በድምቀት የሚከበሩበት ወር ነው።

ህብረተሰቡ  በዓላቱን የጋራ  እሴትን  በጠበቀ መልኩ እንዲያከብር  የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዓሉን  በስኬት ለማክበርም ኮሜቴ በማዋቀር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መብራትና ውሃን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች መቆራረጥ እንዳያጋጥም ከተቋማቱ ጋር በመነጋገር የመፍትሄ አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ በበኩላቸው፣ የተደረገው ዝግጅት  በዓላቱን በሰላም፣ በደስታና በአብሮነት ለማክበር የሚያስችል ነው ብለዋል።

የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማቀናጀት  በዓሉን በስኬት ለማክበር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር አባ ለይኩን ወንድይፍራው በበኩላቸው፣ ጥምቀትና ሌሎችም በዓላት ሀይማኖታዊ ይዘታቸውን ጠብቀው በስኬት መከበር እንዲችሉ በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአሉን አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን በደስታ ለማክበር ተዘጋጅተናል ብለዋል።

"በዓላት በሰላምና በአንድነት እንዲከበሩ የድርሻችንን እየተወጣን ነው" ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሸህ ሐሰን ሐሚዲን ናቸው።


 

በመድረኩ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም