ቀጥታ፡

በክልሉ ለግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን መሳካት የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ሚናው የጎላ ነው

ቦንጋ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ ለግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን መሳካት የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ሚናው የጎላ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የተገዙ የ15 ተሽከርካሪዎች ርክክብ ዛሬ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል። 


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና ግብርና ቢሮ ሀላፊ ማስረሻ በላቸው ተሽከርካሪዎቹን ሲያስረክቡ እንደገለጹት፣ በክልሉ የግብርና ሥራ ውጤታማነትን በማሳደግ የግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ሥራ ስኬታማ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቷል።

በዚህ ሂደትም የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች ባሉ ከ330 በላይ ቀበሌዎች 1 ነጥብ 5 ሚሊየን አባወራና እማወራዎች በፕሮግራሙ ታቅፈው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ በተለይ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥራን ለማሳካትና በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት የመስኖ አውታሮችን በመገንባት አርሶ አደሩ ዘመናዊ አሰራር እንዲከተል እያደረገ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም አርሶ አደሩ ካመረተው ምርት ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ዘመናዊ መጋዝኖችን በመገንባትና ሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎችን በማከናወን እየደግፈ መሆኑንም አንስተዋል።

ፕሮግራሙ የግብርና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ተግባራትን የማሳለጥ ግብ እንዳለውና በፕሮግራሙ ለታቀፉ ወረዳዎች የተለያዩ ግብዓቶችን በድጋፍ የማጠናከር ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ለስራው ስኬታማነት በፕሮግራሙ ለታቀፉ ወረዳዎች ዛሬ 15 ተሽከርካሪዎች ርክክብ መደረጉን ጠቅሰው፣ የግብዓት አቅርቦት ሥራው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የተለገሱ ተሽከርካሪዎችን ለግብርና ሥራና ለፕሮግራሙ ዓላማ ማስፈፀሚያ ብቻ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበው፣ ለዚህም ተገቢ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል። 


 

በፕሮግራሙ ከታቀፉ መዋቅሮች መካከል የኮንታ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ሥራ መምሪያ ሀላፊ ፋንታሁን አስፋው ፕሮግራሙ ከ62 በላይ ቀበሌዎች ግብርናን በማዘመን የአርሶ አደሩን ምርታማነት እያሳደገና ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰሜን ቤንች ወረዳ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ ቡዙአብ ደምመላሽ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በወረዳው በፕሮግራሙ በታቀፉ ቀበሌዎች ኩታ ገጠም እርሻ እየተስፋፋ ነው።


 

የተደረገው ድጋፍ ከዚህ ቀደም ልማቱን ስኬታማ ለማድረግ በሚደረግ እንቅስቃሴ ይገጥም የነበረን የተሽከርካሪ ችግር በመፍታት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይረዳል ብለዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም