ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የስሪላንካ አምባሳደር አሰናበቱ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የስሪላንካ አምባሳደር አሰናበቱ
አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የስሪላንካ አምባሳደር ታሻንታ ኩማራሲሪን አሰናብተዋል።
ተሰናባቹ የስሪላንካ አምባሳደር ታሻንታ ኩማራሲሪ ሲሪላንካ እና ኢትዮጵያ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ዘመናዊ ግንኙነት እአአ በ1972 መመስረቱን ገልጸው፤ አሁን ላይ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያላቸው ግንኙነት ማደጉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በኢነርጂ፣ በግብርና እና በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት መጎልበቱን ጠቁመዋል፤ 200 የሚጠጉ ሲሪላንካውያን በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ሲሪላንካ ግንኙነታቸውን ለማስፋት በርካታ እድሎች እንዳላቸውም ነው ጨምረው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ስሪላንካ ዋና ከተማ ኮሎምቦ ቀጥታ በረራ እንዲጀምር በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር የበለጠ ለማሳደግ፣ ለንግድ ልውውጥ፣ ለአየር መንገድ የጭነት አገልግሎት፣ ቱሪዝምንና እንደ ኢነርጂ ያሉ ሌሎች ዘርፎችንም እንደሚያስፋፋ አመላክተዋል።
በተጨማሪም በግብርና፣ የከበሩ ድንጋዮችና ጌጣጌጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።