ቀጥታ፡

የወረዳው አርሶ አደሮች ያረጁ የቡና ዛፎችን በመጎንደልና በአዲስ በመተካት ምርታማነታቸውን እያሳደጉ ነው

መቱ፤ ጥር 6/2018 (ኢዜአ)፡-በኢሉአባቦር ዞን የያዮ ወረዳ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ያረጁ የቡና ዛፎችን በመጎንደልና በአዲስ በመተካት ምርታማነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ገለጹ። 

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የሥራ ሀላፊዎች በኢሉአባቦር ዞን ያዮ ወረዳ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ተመልክተዋል።

በወረዳው ቡና አምራች አርሶ አደሮች መካከል ሼህ አብዱራህማን አብዱሰላም እና አቶ ጋሻው አማረ ያረጁ የቡና ዛፎች  ምርታማነታቸው በመቀነሱ ከቡና ምርቱ  የድካማቸውን ያህል ውጤት ሳያገኙ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በግብርና ባለሙያዎች በተደረላቸው ሙያዊ ድጋፍ ያረጁ ቡናዎችን በመጎንደል ምርታማነታቸውን ማሻሻል መቻላቸውን ገልጸዋል።

ያረጁ የቡና ዛፎችን ከመጎንደል ባለፈም ምርታማነታቸው የተሻሻለ የቡና ዝርያዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው  ተፈሪ፣ በዞኑ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ከማቅረብ ባለፈ በቡና ጉንደላ ላይ ያተኮረ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የቡና ምርታማነትን ለማሳደግም ያረጁ የቡና ዛፎችን የመጎንደል እና ነቅሎ በአዲስ የመተካት ተግባራት በየዓመቱ በመደበኛነት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ የቡና ምርት መጠንና የጥራት ደረጃን በማሳደግ በገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የቡና ተክል ዝርያ ማሻሻል ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ናቸው።


 

አቶ ጌቱ እንደገለጹት በተያዘው በጋ ወቅት በክልሉ በ115 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ጉንደላና በ62 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ያረጁ የቡና ተክሎችን በአዲስ የመተካት ሥራ ይከናወናል ብለዋል። 

የቡና ተክል እድሳት ስራው የቡና ምርት መጠንና ጥራት ደረጃ እንዲጨምር በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘው ውጤት ይበልጥ እዲያድግ የሚረዳ መሆኑንም አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም