ቀጥታ፡

በክፍለ ከተማው እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ የከተማውን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስም እድል ፈጥሯል

ሸገር ፤ጥር 6/2018 (ኢዜአ)፡- በሸገር ከተማ አስተዳደር መልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ማራኪ ከባቢን ከመፍጠር ባለፈ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እድል መፍጠሩን የክፍለ ከተማው አስተዳደር ገለፀ።

የኮሪደር ልማት ስራው ለክፍለ ከተማው ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ያስቻለ መሆኑም ተገልጿል።


 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክፍለ ከተማው ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ገመቺስ መርጋ፣ በክፍለ ከተማው እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ የአካባቢውን ገጽታ በሚቀይር መልኩ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በክፍለ ከተማው በሁለት አቅጣጫ ስምንት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ሲሆን ስራውም ለዘመናዊ ከተማ የሚመጥን አካታች በሆነ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

እስካሁን የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራም የከተማውን ውበት ከማጉላት ባለፈ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚረዱ መሰረተ ልማቶችም የተዘረጉበት መሆኑን ተናግረዋል።

በኮሪደር ልማት ስራው የእግረኛ፣ የሳይክል፣ በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የማረፊያ ስፍራዎችን ያካተተ ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረጊያ ስፍራዎች፣ የማህበረሰብ መጸዳጃ ቤቶች እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስራው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል በላቸው ደገፋ በአካባቢያቸው የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራው ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

እስካሁን በተሰራው የኮሪደር ልማት ስራ ከተማዋን ከማስዋብ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም መንገድን ጨምሮ ይታዩ የነበሩ የመሰረተ ልማት ችግሮች እየተፈቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራው በታቀደው መሰረት እንዲቀጥል የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ሁሉ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።


 

በኮሪደር ልማት ስራው የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ዳምጦ በሹ እና ፍቃዱ አበራ ስራው ከተማዋን ከማዘመን ባለፈ ለበርካታ ሰዎች ስራ መፍጠሩን አውስተዋል።


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም