ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ ዘመናዊ የችርቻሮ ንግድን ለማስፋፋት ዕድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ጥር 6/2018 (ኢዜአ)፡-የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ ዘመናዊ የችርቻሮ ንግድን ለማስፋፋትና የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ ዕድል መፍጠሩን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለፁ።

በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚገኘው ኩዊንስ ሱፐርማርኬት የንግድ ስያሜን ከነሙሉ አሰራሩ የመጋራት (የፍራንቻይዝ) እና የአቅርቦት አጋርነት ስምምነት ከዓለም አቀፍ የችርቻሮ ንግድ ተቋም ካርፎር (Carrefour) ጋር ተፈራርመዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ተጨባጭ ውጤቶችን እያስገኘ ነው።

በማሻሻያው የችርቻሮ ንግድ ለውጭ ገበያ ክፍት መደረጉን አስታውሰው፤ ይህን ተከትሎ አቅም ያላቸው ተቋማት እየመጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ ዘመናዊ የችርቻሮ ንግድን ማሳለጥ የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ተናግረዋል።

የፈረንሳዩ ካርፎር ግሩፕም የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሚድሮክ ግሩፕ ይህን ዕድል በመጠቀም ላደረገው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

ተቋማቱ ያደረጉት ስምምነት ኢትዮጵያዊያን ጥራት ያላቸው ምርቶችን እንዲያገኙና የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ እንዲተዋወቁ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

በስምምነቱ መሠረት 13 የኩዊንስ ሱፐርማርኬት ቅርንጫፎች ወደ ካርፎር ብራንድ የሚቀየሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያዎቹ መደብሮች እ.ኤ.አ በ2026 አጋማሽ ሥራ ይጀምራሉ ተብሏል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የሀገር ውስጥ ምርትን ከዓለም አቀፍ የንግድ እና የጥራት ደረጃዎች ጋር ለማጣጣም እንደሚረዳ አንስተዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዕድል የሚከፍት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በስምምነቱ መሰረት ነባር የኩዊንስ ሱፐር ማርኬቶችን በካርፎር ስያሜ ከመቀየር ባሻገር በተለያዩ የሀገሪቷ ከተሞች ቅርንጫፎችን የማስፋፋት ዕቅድ መያዙን አመልክተዋል፡፡

ሚድሮክ የሚያመርታቸውን እንደ ቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ ቅመም ፣አበባና ፍራፍሬ ያሉ ምርቶች በካርፎር ዓለም አቀፍ መረብ አማካኝነት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የችርቻሮ ንግድን ለማስፋፋትና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል።

የካርፎር ኢንተርናሽናል ፓርትነርሺፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፓትሪክ ላስፋርጉስ በበኩላቸው፤ ነባር የኩዊንስ ሱፐርማርኬቶችን በፍጥነት በካርፎር ስያሜ ስር ከመቀየር በዘለለ እስከ 2028 ድረስ 17 ተጨማሪ የችርቻሮ መደብሮችን ለመክፈት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡


 

በዘርፉ ሚድሮክ ያለውን የላቀ እውቀትና የካርፎርን ዓለም አቀፍ ልምድ በማቀናጀት ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች ጥራት ያላቸው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እንሰራለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ገልጸው፤ በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በርካታ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች እንዲከፈቱ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።

ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በቀላሉ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ኢትዮጵያ ታዋቂ የሆነችባቸውን ቡናን የመሳሰሉ ምርቶች ለዓለም ገበያ በብዛትና በከፍተኛ ጥራት እናቀርባለን ብለዋል።

ካርፎር ግሩፕ በ40 ሀገራት መደብሮች እንዳሉት ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ሥራ መጀመሩ በዓለምአቀፍ ገበያ የአገሪቷን ምርቶች ያስተዋውቃል ብለዋል።

ካርፎር በዓለም ዙሪያ ከ15ሺ በላይ መደብሮች ያሉት ሲሆን፤ እኤአ በ2024 ብቻ 94 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ ያስመዘገበ ግዙፍ ኩባንያ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም