የባህር በር ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ግዴታችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ግዴታችንን እንወጣለን
ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ የዘለቀው የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ ሀገራዊ ግዴታችውን እንደሚወጡ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
ኢዜአ በወላይታ ሶዶ ያነጋገራቸው የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የትውልዱ የዘመናት ጥያቄ ቢሆንም በአደባባይ ሲነሳ አልነበረም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የራሷ የባህር በር እንዲኖራት የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው የተጀመረው ጥረት ከግብ እንዲደርስ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተባባሪ አቶ ዳንኤል ሽቱ፤ የባህር በር ጉዳይ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት የትውልዱ የመብት ጥያቄ መሆኑን አንስተዋል።
ፓርቲያቸው በማንፌስቶው የባህር በር ጉዳይን አካቶ ለምላሹ እየሰራ መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያን ዳግም የባህር በር ባለቤት ለማድረግ የተጀመረው ጥረት የሚደገፍና የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ከግብ እንዲደርሱ ፓርቲያቸው በቁርጠኝነት ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የጋራ በሚያደርጉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከመንግስት ጎን በመሆን እየደገፉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት ፓርቲ (ኢዴህ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የወላይታ ዞን አስተባባሪ አቶ ወልዴ ዳና ናቸው።
መንግስት በፈጠረው ምቹ ምህዳር ከመንግስት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ያሉት አቶ ወልዴ፣ የባህር በር የማግኘት ጥያቄም የሀገርንና የህዝብን ቀጣይ እጣ ፋንታና የልማት ተጠቃሚነትን የሚወስን በመሆኑ ከፍተኛ ቅንጅትን ይጠይቃል ብለዋል።
በሴራ ፖለቲካ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ የተደረገበት መንገድ አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ የባህር በር ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ደማቸውን የገበሩበት የግዛት አንድነቷን የሚያጠናክር የወል ትርክታችን ነው ብለዋል።
የባህር በር ጥያቄ የዘመናት የትውልድ ጥያቄ መሆኑን አስታውሰው ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ እንደፓርቲ ያላቸውን የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ወደ ጎን በመተው በጋራ መቆማቸውንም ገልጸዋል።
በሀገርና በህዝብ ጥቅም ላይ ልዩነትን ወደጎን በማለት የባህር በር ጥያቄን ጨምሮ ሀገራዊ እድገትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ፓርቲው የበኩሉን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
በአዲስ ትውልድ ፓርቲ የወላይታ ዞን ሰብሳቢ አቶ ተፈሪ ሞላ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር እየተተገበሩ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፓርቲያቸው ለህዝብና ለሀገር ጥቅም የሚሰሩ ልማቶችን እንደሚደግፍ ጠቁመው፣ የባህር በር የማግኘት ጥያቄም ፓርቲው በግንባር ቀደምነት የሚደግፈውና የሚታገልለት አጀንዳ መሆኑን አስረድተዋል።