ቀጥታ፡

የአፋር ባህላዊ ህግ (ማድዓ)ን በዩኔስኮ ማስመዝገብ የሚያስችል መረጃ ለመሰነድ ያለመ ኮንፍረንስ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦የአፋር ባህላዊ ህግ (ማድዓ)ን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ማስመዝገብ የሚያስችል መረጃ ለመሰነድ ያለመ ኮንፍረንስ በአፋር ክልል ሠመራ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ።

ኮንፍረንሱ ከየካቲት 03 እስከ 05 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል። 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የአፋር ክልል ስፖርት፣ ወጣቶችና ባህል ቢሮ ሃላፊ ሀሚድ ዱላ እና የአፋር ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀቢብ መሐመድ ኮንፍረንሱን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። 

የቢሮ ሃላፊው አቶ ሀሚድ ዱላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ማድዓ ከሀገር በቀል እውቀቶች አንዱ ሲሆን፤ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያገለገለ የሚገኝ ነው።


 

ይህ ሀገር በቀል እውቀት ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት በህዝቦች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም ይሄንን ትልቅ እሴት በዩኔስኮ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ለማስመዝገብ ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ማድዓን በዩኔስኮ ማስመዝገብ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የማይዳሰስ ቅርስ እንዲሆንና የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም  የበለጠ  እንዲነቃቃ ያግዛልም ብለዋል።

የአፋር ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀቢብ መሐመድ  በበኩላቸው፤ ኮንፍረንሱ ባህላዊ መሪዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የአፋር ሱልጣን ፣ የአፋር ልሂቃን እና ሌሎችም የሚሳተፉበት መሆኑን ገልጸዋል።

በኮንፍረንሱ የአፋር ባህላዊ ህግ (ማድዓ)ን የተመለከቱ እሴቶች ላይ ውይይት የሚደረግበት መሆኑን ተናግረዋል።

የአፋር ማህበረሰብ ከዘመናዊ የህግ ስርዓት በተጨማሪ ባህላዊ  ዳኝነት ስርዓት ያለው ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም