ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው
ጅግጅጋ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ሀገራዊ ምክክሩ ያላግባቡ ጉዳዮች ላይ በሰለጠነ መንገድ በመምከር ለሀገር ዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና ብሄራዊ መግባባት መፍጠርን ዓላማ አድርጎ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከዝግጅት እስከ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምእራፍ ድረስ ለዋናው ምክክር ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
በተለይም በአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ላይ ዜጎች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በመምከር እና አጀንዳ በመስጠት በንቃት መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከመነሻው የምክክር ሂደቶቹን አካታች እና አሳታፊ በማድረግ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሲያሳትፍ ቆይቷል ብለዋል።
በምክክሩ ዙሪያም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ እያከናወነ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በዚህም ሀገራዊ ምክክሩ በሀገሪቱ የነበሩ ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አብዱራህማን መሀመድ፤ ሀገራዊ ምክክሩ የጋራ አጀንዳ በማሰባሰብ፤ ችግሮችን በምክክር በመፍታትና አዲስ ባህል ለማዳበር ያግዛል ብለዋል።
ይህም በሀገሪቱ የጋራ ትርክት ለመገንባት በሚደረገው ጥረቶች የማይናቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አቶ አደን ዩሱፍ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሀገሪቱ እያከናወነ ያለው የምክክር ሂደቶች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማካተት የተከናወነ በመሆኑ የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ያሉ አለመግባባቶችን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት የምክክር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።
አቶ መላኩ ባልቻ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገሪቱ የእድገት ጉዞ የላቀ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ በተለይም መግባባትን በመፍጠር የኢትዮጵያን ብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ያስችላል ብለዋል።
ሠላም ለሀገሪቱ እድገት ወሳኝ መሆኑን ተናግረው፤ በተለይም የታቀዱ የልማት ሥራዎችን ከግብ ለማድረስ ሀገራዊ ምክክሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።