ቀጥታ፡

ዕድሜ  ያልገደበው የልማት አርበኝነት 

ዕድሜ ያልገደበው የልማት አርበኝነት 

ብርቱዎች ነገን በማሰብ ሁሌም ታትረው ይሰራሉ፤ ይደክማሉ፤ ይጥራሉ…ለቀጣዩ ትውልድም ጥሪት በማስቀመጥ አሻራቸውን ያኖራሉ።

አገር የምትገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ ነው። “አባት ያበጀው፤ ለልጅ ይበጀው” እንደሚባለው ልጆች ከአባቶቻቸው ያገኙትን ጥሪት በአዲስ እውቀትና አሰራር ለአገር እድገት በሚበጅ መልኩ አጠናክረው መጠቀማቸው አይቀርም። 

“ዕድሜ ጸጋ ነው” የሚለው አባባል አንዳንዴ በዕድሜ ብንገፋም ጠንክረን ከሰራን ብዙ ነገር እናያለን ከሚለው ጋር የተያያዘ ነው። በሰቆጣ ከተማም እድሜ ሳይገድባቸው በልማት ውጤታማ የሆኑ ግለሰቦች ለዚህ ማሳያ ናቸው።

የከተማዋ ነዋሪ የ67 ዓመቱ አቶ ብርሃኑ አወቀ እና የ83 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አቶ ታደሰ አዳነ ዕድሜያቸው ቢገፋም ጠንክሮ ከተሰራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልና ዕድሜ ጸጋ ሆኖ ብዙ ለውጥ ማየት እንደሚቻል ማሳያ ናቸው።

ግለሰቦቹ ከዕድሜ ብዛት ጉልበቴ ደከመ፣ አይኔ ፈዘዘ፣ እጄም ተሳሰረ…ሳይሉ ጊዜያቸውን በደን፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ በማሳለፍ ለወጣቶች የልማት አርአያነት ያለው ተግባር እየፈጸሙ ነው።

አቶ ብርሃኑ አወቀ በሰቆጣ ከተማ ዳርቻ የሚገኝ አለቱ ያገጠጠና የተራቆተ አካባቢን ከሌላ አካባቢ ለም አፈር በማምጣትና በመደልደል አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ደን በማልማት ውጤታማ ስራ እያከናወኑ ነው።


 

ከመንግስት ሥራ በጡረታ ከወጣሁ ጀምሮ ጠንክሬ በመስራት የምለወጥበትን ሥራ ማሰብ ስነበረብኝ፤ የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ለዘመናት የቆየን ጭንጫ መሬት ጠርጌና ደልድዬ ማልማት ችያለሁ ይላሉ ወደኋላ መልስ ብለው የተነሱበትን ሁኔታ ሲያስታውሱ።

ግማሽ ሄክታር በማይሞላ መሬት ላይ  ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ዘይቱና፣ ጌሾ፣ ቡና፣ ማንጎና አቮካዶ አልምተዋል።

በተጨማሪም ቆስጣ፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመንና ሽንኩርት በማምረት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ጥሪት አፍርተዋል።


 

ጊዜን በአግባቡ ተጠቅሞ ተግቶ መስራት ከተቻለ ሀብት ማፍራትና  ህይወትንም መለወጥ እንደሚቻል የገለጹት አቶ ብርሀኑ፣ ወጣቱም ከእሳቸው የሥራ ትጋት በመማር በአካባቢው ያለውን ፀጋ ለይቶ በማልማት ሊጠቀም ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።

ሌላው የ83 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አቶ ታደሰ አዳነ ባለፉት 18 ዓመታት በተሰማሩበት የአትክልትና ደን ልማት ሥራ የአካባቢያቸውን ገጽታ ቀይረዋል።

የዕድሜ ዘመናቸውን በውትድርናና በመንግስት ሠራተኝነት በማገልገል ሃገራዊ ግዳጃቸውን ሲወጡ ነው የቆዩት።


 

ከመንግስት ሥራ በጡረታ ከተገለሉ በኋላም ቤት ውስጥ መቀመጥን አልመረጡት። አካፋና ዶማቸውን ይዘው ባላቸው ትንሽ መሬት ላይ ጌሾ፣ ዘይቱና እና ማንጎ በማልማት ምርቱን ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል።

በአካባቢያችን ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ ለይተን ማልማት ከቻልን ድህነትን ማስወገድ የሚከብድ አይሆንም ያሉት አቶ ታደሰ፣ የተራቆተና በጎርፍ የተጎዳን መሬት በማልማት አካባቢውን ሳቢና ማራኪ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።

ወጣቱም ከእሳቸው አርአያነት ያለው ተግባር በመማር በአካባቢው እጁ ላይ ባለ ሀብት ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በተግባር ማሳየት እንዳለበት መክረዋል።


 

የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ደሳለኝ አዳነ እንደገለጹት፤ በብሔረሰብ አስተዳደሩ 24ሺህ 847 አርሶ አደሮች በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተዋል።

ከአርሶ አደሮቹ መካከል ዕድሜ ሳይገድባቸው ወደ ልማት የገቡ አረጋዊያን እያከናወኑት ያለው የግብርና ልማት ሥራ ለወጣቱ ትልቅ ትምህርት እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ከእነሱ ልምድ በመውሰድ በዞኑ ወጣቶች፣ ሴቶችና አረጋዊያን በጓሮና ባላቸው መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለሙ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ይህም በዞኑ የሚስተዋለውን የስርዓተ ምግብ ችግር ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም