ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን
አዳማ ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት ተጠናቆ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በምክክር ሂደቱ ውስጥ የምናደርገውን ተሳትፎ እናጠናክራለን ሲሉ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ሀዳ ሲንቄዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ11 ክልሎች እና 2 የከተማ አስተዳደሮች፣ በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለድርሻ አካላት ዘንድ አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ሰርቷል።
በአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፉም በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መሳተፍ የሚገባቸው ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ የመከሩ ሲሆን በሂደቱ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓት ውስጥ ትልቅ ሚና ያላቸው ባለድርሻ አካላትም መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልልም በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በስፋት ተሳትፎ ካደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ሃዳ ሲንቄዎች ይጠቀሳሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዳማ ከተማ የሚገኙ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ሃዳ ሲንቄ ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት ተጠናቆ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው በምክክር ሂደቱ ውስጥ የሚወጡትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
በአዳማ ከተማ የአባገዳ ክፍለ ከተማ ባህላዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ፈይሣ መገርሳ እንደገለፁት፤ሀገራዊ ምክክሩ የነበሩ ቁርሾዎችና ቅራኔዎች የሚፈቱበት ሁነኛ መፍትሔ ነው።
እስካሁን በተደረጉ የምክክሩ ሂደቶችም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃዳ ሲንቄዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በአዳማ በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ላይ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያግዙ ጠቃሚ ሀሳቦችን ማቅረባቸውን አስታውሰው፤ አሁንም ሂደቱ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የምክክሩ ሂደት ውጤታማ እንዲሆን የድርሻችንን እየተወጣን ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ተወግደው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እስከ ፍጻሜው ተሳትፏችንን እናጠናክራለን ብለዋል፡፡
የሀገር ሽማግሌው አቶ ድሪባ ጫላ በበኩላቸው፤ በክልል ደረጃ በአዳማ ከተማ በተካሄደው የምክክር ምዕራፍ ተሳትፈው አብሮነት እና አንድነትን የሚያጠናክሩ ሀሳቦች ማንሳታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶችን በመጠቀም በየአካባቢው ላሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ አመልክተው የምክክሩ ሂደት እንዲሳካ እንደ ሀገር ሽማግሌ ሚናችንን እናጠናክራለን ብለዋል።
በቀጣይ በሚካሄደው ብሔራዊ ምክክር የሚሳተፉ አካላት ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ሀገር እንድትሆንና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሀሳቦች ላይ ማተኮር አለባቸው ያሉት ደግሞ የአገር ሽማግሌ አቶ ጥላሁን ራጎ ናቸው።
ምክክሩ ችግሮቻችንን የምንፈታበት፣ የወደ ፊቷ ኢትዮጵያ የተሻለች እና ለሌሎች ምሳሌ እንድትሆን ምክክሩ ውጤት እስኪያመጣ ድረስ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ሃዳ ሲንቄ ብርቄ ከበደ በበኩላቸው፤ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደረግ መፍትሄ ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ሁሉም ለምክክሩ ስኬታማነት የድርሻውን ማጠናከር አለበት ብለዋል።