ቼልሲ እና አርሰናል በካራባኦ ዋንጫ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቼልሲ እና አርሰናል በካራባኦ ዋንጫ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ካራባኦ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር የግማሽ ፍፃሜ መርሃ ግብር ቼልሲ እና አርሰናል ዛሬ ይጫወታሉ።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ይካሄዳል።
በሩብ ፍጻሜው ቼልሲ ካርዲፍ ሲቲን ፣ አርሰናል ክሪስታል ፓላስን በማሸነፍ የመጨረሻ አራት ውስጥ ገብተዋል።
ቼልሲ የካራባኦ ዋንጫን አምስት ጊዜ አንስቷል። የለንደን ጎረቤቱ አርሰናል ሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ለመጨረሻ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ የነበረው እ.አ.አ በ2014/15 የውድድር ዓመት ነው።
የሰሜን ለንደኑ አርሰናል እ.አ.አ 1992/93 ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል።
ቡድኖቹ በካራባኦ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱ ክለቦች በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪው ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
እ.አ.አ በ2018 በተመሳሳይ በግማሽ ፍጻሜ ተገናኝተው አርሰናል በድምር ውጤት 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል።
መድፈኞቹ በፍጻሜው በማንችስተር ሲቲ 3 ለ 0 ተሸንፈው ዋንጫውን አጥተዋል።
አዲሱ የቼልሲ ሊያም ሮሲኒየር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ።
የሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታ ጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ትናንት በካራባኦ ዋንጫ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ኒውካስትል ዩናይትድን 2 ለ 0 አሸንፏል።