ቀጥታ፡

የአፍሪካ ዋንጫን የወርቅ ጫማ ማን ይወስዳል?

በሞሮኮ አስተናጋጅነት ታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወደ መገባደዱ ላይ ደርሷል።

የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

ሴኔጋል ከግብጽ ምሽት አንድ ሰዓት፣ ናይጄሪያ ከሞሮኮ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ለፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው።


 

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ እስከ አሁን በተደረጉ 48 ጨዋታዎች 119 ግቦች ከመረብ ላይ አርፈዋል።

በየጨዋታው በአማካይ 2 ነጥብ 48 ግቦችን ተቆጥረዋል።

119 ግቦች ኮትዲቯር ባዘጋጀችው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ከተቆጠረው ተመሳሳይ የግብ መጠን ተስተካክሏል። 

35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ሆኖ እንደሚጠናቀቅ እርግጥ ነው።

ጨዋታዎቹ በጎል የታጀቡ እና አዝናኝ እንቅስቃሴ ተደርጎባቸዋል።


 

ከዋንጫው ፉክክር ባልተናነሰ የኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱ ጉዳይ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ትኩረት ስቧል።

በውድድሩ ላይ ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው የሞሮኮው የክንፍ መስመር ተጫዋች ብራሂም ዲያዝ በአምስት ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል።

የናይጄሪያው ቪክቶር ኦሲሜን እና የግብጹ መሐመድ ሳላህ በተመሳሳይ አራት ጎሎችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ይከተላሉ።


 

የሞሮኮው አዩብ ኤል ካቢ እና የናይጄሪያው አዴሞላ ሉክማን በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን አስቆጥረዋል። 

ዛሬ ናይጄሪያ እና ሞሮኮ በሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የቪክቶር ኦሲሜን እና ብራሂም ዲያዝ ፍጥጫ ይጠበቃል።


 

ሴኔጋል ከግብጽ በሚያከናውኑት ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር የግብጹ መሐመድ ሳላህ የሚጠበቅ ይሆናል።

የወርቅ ጫማውን ማን ይወስዳል? ለሚለው ጥያቄ ቀሪ አራት ጨዋታዎች ምላሽ ይሰጣሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም