ኃያላኑን ያገናኘው የአፍሪካ ዋንጫ ተጠባቂ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር - ኢዜአ አማርኛ
ኃያላኑን ያገናኘው የአፍሪካ ዋንጫ ተጠባቂ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር
አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ሴኔጋል ከግብጽ ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ በታንጀር ስታዲየም ይጫወታሉ።
በሩብ ፍጻሜው ሴኔጋል ማሊን፣ ግብጽ ኮትዲቯርን በማሸነፍ የመጨረሻ አራት ውስጥ ገብተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ሴኔጋል በሶስቱ ድል ሲቀናት ግብጽ ሁለት ጊዜ አሸንፋለች።
እ.አ.አ በ1986 ግብጽ ባዘጋጀችው 15ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ሴኔጋል በቲርኖ ዩም ጎል 1 ለ 0 አሸንፋለች።
በሀገራቱ የእርስ በእርስ ግንኙነት ውስጥ በዋናነት የሚነሳው ካሜሮን እ.አ.አ በ2021 ባዘጋጀችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዋንጫ ለማንሳት የተፋለሙበት ነው።
ሴኔጋል በመለያ ምት 4 ለ 2 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካን ዋንጫ አንስታለች።
ግብጽ ለመጨረሻ ጊዜ ሴኔጋልን በአፍሪካ ዋንጫው ያሸነፈችው እ.አ.አ በ2006 ባዘጋጀችው 25ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው።
በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው ግብጽ በአህመድ ሀሰን እና አሚር ዛኪ ግቦች 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች። ማማዱ ኒያንግ ለሴኔጋል ብቸኛውን ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።
ግብጽ በፍጻሜው ኮትዲቯርን በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች። ውድድሩን ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ስኬታማዋ ሀገር ናት።
ከቅርብ ዓመታት በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ተፎካካሪነታቸው እያደገ የመጣው ሁለቱ ሀገራት ለፍጻሜው ለማለፍ ጠንካራ ፍልሚያ ያደርጋሉ።
በሊቨርፑል ማልያ አንድ ላይ የተጫወቱት ሳዲዮ ማኔ እና መሐመድ ሳላህ በጨዋታው ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ናይጄሪያ ከሞሮኮ ምሽት አምስት ላይ በፕሪንስ ሙላይ የሚያደርጉት ጨዋታም ተጠባቂ ነው።
ናይጄሪያ በሩብ ፍጻሜው አልጄሪያን፣ ሞሮኮ ካሜሮንን በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል።
ሀገራቱ በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ ነው።
የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1976 በተካሄደው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው።
በምድብ ሁለት ተገናኝተው ሞሮኮ 3 ለ 1 አሸንፋለች። አህመድ ፋራስ፣ አብደላ ታዚ እና ላርቢ ቼባክ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ሳሙኤል ኦጄቦዴ ለናይጄሪያ ብቸኛውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል። ሞሮኮ ጊኒን በማሸነፍ ብቸኛውን ዋንጫ በወቅቱ አንስታለች።
እ.አ.አ በ1980 በናይጄሪያ በተካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በግማሽ ፍፃሜው ተገናኝተው አዘጋጇ ናይጄሪያ በግማሽ ፍጻሜው በፍሊክስ ኦዎላቢ ግብ 1 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች።
በፍጻሜው ናይጄሪያ አልጄሪያን 3 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።
ብሄራዊ ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ2004 በቱኒዚያ በተካሄደው 24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነበር።
በምድብ አራት ባደረጉት ጨዋታ በዩሱፍ ሃጂ ጎል ሞሮኮ 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ሁለቱ ሀገራት አጠቃላይ አምስት ጊዜ ተገናኝተው ሞሮኮ ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ ናይጄሪያ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቷታል።
ከ22 ዓመታት በኋላ በአህጉራዊው መድረክ የሚገናኙት ሀገራቱ ለተመልካች አዝናኝ እና ተመጣጣኝ ፉክክር ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አራት ግቦችን ያስጠቆጠረው ቪክቶር ኦሲሜን ከናይጄሪያ እና አምስት ግቦችን ከመረብ ጋር በማገናኘት ኮከብ ግብ አግቢነቱን የሚመራው ብራሂም ዲያዝ ከሞሮኮ በጨዋታው ልዩነት ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማሉ።
ተሸናፊ ሀገራት ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት ጥር 9 ቀን 2018 ዓ.ም ይጫወታሉ።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ