በካራባኦ ዋንጫ ማንችስተር ሲቲ ድል ቀንቶታል - ኢዜአ አማርኛ
በካራባኦ ዋንጫ ማንችስተር ሲቲ ድል ቀንቶታል
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ካራባኦ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ኒውካስትል ዩናይትድን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በሴይንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አንቶዋን ሴሜንዮ በ53ኛው እና ራያን ቸርኪ በ98ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።
በጨዋታው ላይ ማንችስተር ሲቲ ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎችን በሚገባ መጠቀሙ ባለድል አድርጎታል።
በአንጻሩ ኒውካስትል ዩናይትድ ግልጽ የግብ እድሎችን አምክኗል።
በጨዋታው ላይ አዲስ ፈራሚው ሴሜንዮ ጥሩ ብቃት ያሳየ ሲሆን የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል።
ውጤቱን ተከትሎ ማንችስተር ሲቲ ወደ ፍጻሜ የማለፍ እድሉን አስፍቷል።
በአንጻሩ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ኒውካስትል ዩናይትድ ውጤቱን የመቀልበስ ጠንካራ የቤት ስራ ይጠብቀዋል።
የሁለቱ ክለቦች የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ሌላኛው የመጀመሪያ ዙር የካራባኦ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር በቼልሲ እና አርሰናል መካከል ነገ ይደረጋል።