ቀጥታ፡

የዳራሮ ባህላዊ እሴቶች ሳይበረዙ የቱሪዝም መስህብነቱን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው 

ዲላ ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦‎የጌዴኦ የዘመን መለወጫ "ዳራሮ" በዓል ባህላዊ እሴቶቹ ሳይበረዙ የቱሪዝም መስህብነቱን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

የጌዴኦ ዘመን መለወጫ በዓል "ዳራሮ ለባህልና ለቱሪዝም ዕድገት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአባ ገዳ መናገሻ በኦዳ ያአ ሶንጎ መከበር ጀምሯል።


 

በዓሉ በመሸጋገሪያው በር "ሁሉቃ"ን በማለፍና የአባ ገዳ ስጦታ "ጉማታ" መስጠትን ጨምሮ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች መከበር የጀመረ ሲሆን በተያዘው ወር መጨረሻ በዲላ ከተማ እንደሚጠቃለል ተመላክቷል።

የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ዳራሮ የጌዴኦ የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፣ ለአባ ገዳ ስጦታ የሚሰጥበት የአደባባይና የአንድነት በዓል ነው።


 

ቂምና ቁርሾ ተወግዶ በይቅርታና በአንድነት ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ መሆኑን አንስተው ‎የዳራሮ በዓል ባህላዊ እሴቶቹ ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲሸጋገሩ እና  የቱሪዝም መስህብነቱን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በዓሉን በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች በየደረጃው ከማክበር ባለፈ ባህላዊ እሴቶችን የማስተዋወቅ ሥራ ከአምና ጀምሮ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዓሉ ሲከበር ባህላዊ ክዋኔዎች የሚካሄድባቸውን ስፍራዎች በመጠበቅ የበዓሉን እሴቶችን ለትውልድ የማሸጋገር ስራ ይጠናከራል ያሉት ደግሞ የቡሌ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ በራቆ በራሶ ናቸው።


 

የዳራሮን ባህላዊ ስርዓቶች ለልማት እና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለማዋል በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የጌዴኦ ብሔር ባህላዊ አስተዳደር መሪ አባ ገዳ ቢፎሚ ዋቆ በበኩላቸው "ዳራሮ" ፍቅር፣ አንድነትና መተጋገዝ የሚጎላበት ነው ብለዋል።


 

የዘንድሮው ዳራሮ በዓልም በዛሬው ዕለትም በአንጋፋው ኦዳ ያአ ሶንጎ መከበር መጀመሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም