ፓርቲው ለብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ በሰጠው ትኩረት የዜጎች ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መጥቷል -አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲው ለብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ በሰጠው ትኩረት የዜጎች ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መጥቷል -አቶ አደም ፋራህ
ቡታጅራ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ብልፅግና ፓርቲ ለብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ በሰጠው ትኩረት የዜጎች ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መምጣቱን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በቡታጅራ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ፓርቲው ለብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ በሰጠው ትኩረት በየክልሉ የዜጎች ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መጥቷል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም የብልፅግና ፓርቲ የኢኮኖሚ የትኩረት አቅጣጫዎች በአግባቡ ተግባራዊ በመደረጋቸው ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
በቡታጅራ ከተማ የሚገኘው የአቮካዶ ፍራፍሬ ማባዣ ማዕከል የአረንጓዴ አሻራ ትግበራን ስኬታማ ከማድረግ በተጨማሪ የግብርናውን ዘርፍ ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ስለመሆኑ መመልከታቸውንም ገልጸዋል።
የአቮካዶ ፍራፍሬ ማባዣ ማዕከሉ ከሀገር አልፎ ለኤክስፖርት የሚሆኑ የፍራፍሬ ምርቶችን በስፋት የማምረትና የማሰራጨት ሥራ እየሰራ እንደሚገኝም ተመልክተናል ሲሉም አክለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ የሆነው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ትግበራ በቤተሰብ ደረጃ ብልፅግናን የማረጋገጥና የምግብ ዋስትናን እውን ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸው፣ በመርሀግብሩ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
መርሀ ግብሩ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙና ገበያን በማረጋጋት በኩልም ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ስለመሆኑም በምስራቅ ጉራጌ ዞን እየተመዘገበ ያለው ውጤት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም መንግስት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም ኢንቨስትመንትን የማበረታታት፣ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት፣ የውጪ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የሆነውና በቡታጅራ ከተማ የሚገኘው የደስታ ጋርመንት የተለያዩ አልባሳትን በጥራትና በፍጥነት በማምረት ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ ለሥራ እድልና ለአካባቢው እድገት እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑንም አንስተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በበኩላቸው፤ በቡታጅራ ከተማ በከተማ ልማት ዘርፍ በተከናወኑ ሥራዎች የተገኘው ውጤት መጠናከር አለበት ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ የፍራፍሬ ልማትን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግን ጨምሮ በሌማት ትሩፋት እየተመዝገበ ያለውን ተጨባጭ ውጤት ማስፋት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የሚገኘው ደስታ ጋርመንት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን የሚያጠናክር ሥራ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ናቸው፡፡
ፋብሪካው በርካታ ወጣቶች በሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረገና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን መደገፍና ማጠናከር ለውጤት እንደሚያበቃ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን አመልክተዋል።